Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ት/ክፍል ከዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት እና ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስትሮኖሚና አስትሮ ፊዚክስ ዲፓርትመንት ጋር በመተባበር ታኅሣሥ 04/2014 ዓ/ም ሥልጠናዊ ወርክሾፕ አዘጋጅቷል፡፡ በወርክሾፑ ማጠናቀቂያም በኢንስቲትዩቱ እንደ ሀገር ከተያዙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በሆነው በጉጌ ተራራ በመገኘት የጣቢያ ምልከታ ተከናውኗል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በወርክሾቹ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስትሮኖሚና አስትሮ ፊዚክስ ዲፓርትመንት በመጡ ባለሙያዎች ‹‹Capacity Building in Astronomy Research for Sustainable Development››፣ ‹‹National Mapping & Testing of Astronomical Sites in Ethiopia›› እና ‹‹Potential of Ethiopia & African Dark Skies for Socio-Economical & Environmental Benefits›› የሚሉ ሦስት የሥልጠና ሰነዶች ቀርበዋል፡፡

በሰነዶቹ የአስትሮኖሚ እድገት በኢትዮጵያ፣ የአስትሮኖሚ ጣቢያዎች መረጣ አስፈላጊነትና ሂደት፣ የአስትሮኖሚ ጣቢያዎች ለሀገር እድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ አንፃር፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መካከል የተፈረመው የጋራ መግባቢያ ሰነድ አፈፃፀም፣ በጉጌ ለማቋቋም የታሰበው የህዋ ምርምር ጣቢያ አዋጭነት ጥናት እና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአስትሮኖሚና አስትሮ ፊዚክስ ዲፓርትመንት ኃላፊ ዶ/ር ሰብሉ ሁምኔ ወርክሾፑ በአስትሮኖሚና ህዋ ሳይንስ ዘርፍ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ፣ በጋራ ለመሥራት መቀራረብን የሚፈጥርና በቀጣይ የጋራ ሥራዎች ላይ ለመመካከር የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጉጌ የተደረገው የጣቢያ ምልከታ ቦታው ለህዋ ምርምር ጣቢያነት ምቹ መሆኑን ለመፈተሽ ከሚደረጉ ቅኝቶችና ጥናቶች አንዱ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሰብሉ የዓየር ሁኔታ፣ የብርሃን ብክለት አለመኖር፣ የመሠረተ ልማት መሟላትና ሌሎችም አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች በጥናቱ ይፈተሻሉ ብለዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ት/ክፍል ኃላፊ ረ/ፕ ወንድማገኝ አንጁሎ እንደገለጹት ት/ክፍሉ በአስትሮኖሚና ህዋ ሳይንስ፣ በኒውክሌር ሳይንስ እና በማቴሪያል ሳይንስ ዐበይት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡ ከትኩረት ዘርፎቹ አንዱ የሆነውን አስትሮኖሚና ህዋ ሳይንስ ለማጠናከር የት/ክፍሉን የሰው ኃይል በትምህርትና ሥልጠና ለመገንባት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመቀናጀት መሥራታችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ያስታወሱት ኃላፊው በቀጣይ ከት/ክፍሉ ጋር የማጣቀሻ ውሎች /Terms of Reference/ በመፈራረም የጋራ ፕሮጀክቶችን የሚሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ት/ክፍሉ በአስትሮፊዚክስ የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራም ያለው በመሆኑ በሥርዓተ ትምህርት ቅኝትና ተማሪዎች የኢንስቲትዩቱን መረጃዎች ተጠቅመው የመመረቂያ ጽሑፋቸውን እንዲያዘጋጁ በማድረግ በኩል በጋራ መሥራታቸው ትልቅ እገዛ የሚኖረው ነው ብለዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ አብርሃም በበኩላቸው ወርክሾፑ ወደፊት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ለሚኖረው የጋራ ሥራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረው ት/ክፍሉ በአስትሮኖሚና ህዋ ሳይንስ መስክ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ኮሌጁ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስትሮኖሚና አስትሮ ፊዚክስ ዲፓርትመንት ኃላፊና ባለሙያዎች እንዲሁም የፊዚክስ ት/ክፍል ቅድመና ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት