Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ የ2013 ዓ/ም የሥራ አፈጻጸምን መሠረት በማድረግ በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ከዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና የካውንስል አባላት ጋር ከታኅሣሥ 7-9/2014 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት እንደገለጹት ከ2012 ዓ/ም 2ኛ መንፈቀ ዓመት ጀምሮ ባለው ሂደት ምንም እንኳን በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የቅድመ ምረቃ ትምህርት የተቋረጠ ቢሆንም መልሶ ለማስጀመርና ክፍለ ጊዜያትን ለማካካስ ዕቅዶች ተነድፈው ኅዳር/2013 ዓ/ም የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መንገድ ተመራቂ ተማሪዎች ገብተው ተምረው በጥር ወር 2013 ዓ/ም ለመመረቅ በቅተዋል፡፡ በማስከተልም ሌሎች 2ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ተማሪዎች እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በሂደቱ ከኮሮና ቫይረስ ባሻገር በሀገራዊ ምርጫ ምክንያት የተወሰኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት ቢባክኑም 1ኛ እና 2ኛ ዓመትና ተመራቂ ተማሪዎችን ክረምቱን ጨምሮ በማስተማር ከ6 ሺህ በላይ የቅድመ ምረቃ፣ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን መስከረም 29/2014 ዓ/ም ማስመረቅ መቻሉን እንዲሁም የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ሳይቋረጥ በተከታታይ መሰጠቱን በአሁኑ ወቅትም የትምህርት ሂደቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ሥራዎች ሳይቋረጡ መከናወናቸውን እንዲሁም ኮቪድን ከመከላከል ጀምሮ በርካታ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች መሠራታቸውን፣ የተለያዩ የምርምር ሲምፖዚየሞች መካሄዳቸውንና ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ዜጎች የደመወዝ፣ የደም፣ የቁሳቁስና አልባሳት ድጋፎች እና ሌሎች ተግባራት መከወናቸውን ዶ/ር ዳምጠው በሪፖርቱ አመላክተዋል፡፡

የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ የተለያዩ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በዝርዝር ተነስተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ሠራተኞች ምደባ ጉዳይ፣ የተሻሻሉ መመሪያዎችን፣ አዋጆችንና ሕጎችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ የማድረግና የማስተዋወቅ ክፍተት፣ የቅሬታ ምላሽ አሰጣጥ መዘግየት፣ በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተወሰኑ ኃላፊዎች ተግባብተው ያለመሥራት ሁኔታ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍተት፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት ተደራሽነት ጉዳይ፣ የሳውላ ካምፓስ የመማሪያ ክፍል፣ የመምህራንና የአስተዳደር ቢሮዎች፣ የተማሪዎች ማደሪያና የአጥር ግንባታ ጉዳይ፣ የICT አገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት፣ የመምህራን መኖሪያ ቤት ጉዳይ፣ የቢሮ እጥረትና አደረጃጀት ለተቀላጠፈ አገልግሎት ምቹ አለመሆን፣ የደንብ ልብስና የጽዳት ዕቃዎች በወቅቱ አለመቅረብ፣ ሥርዓተ ትምህርትን ከማስማማት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ ጥናትና ምርምሮችን ወደ ፕሮጀክትነት ከማሳደግና ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ያሉ ክፍተቶች፣ የመምህራን የውጪ ሀገር የትምህርት ዕድል የማስተናገድ ሁኔታ፣ የመምህራን መኖሪያ ቤት አበል መጠን ማነስ፣ የቤት መሥሪያ ቦታ የማግኘት ሁኔታ፣ በሶሻል ሚዲያዎች ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ በሚያጎድፉ አካላት ላይ ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችና የመሳሰሉ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና የመፍትሄ ሀሳቦች ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች መከፈታቸው፣ የተማሪ ቅበላ ሁኔታ፣ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎቶች መልካም መሆናቸውን ተናግረው ምርምርን ወደ ፕሮጀክት ቀይሮ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ እና የማኅበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይም ከዩኒቨርሲቲው ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የቦርዱ ም/ሰብሳቢ አክለውም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተገቢ መረጃዎች ለዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ግልጽ መደረግ እንዳለባቸው እና ሠራተኞች ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የግዢ ጉዳይን አስመልክቶ ብዙ ቅሬታዎች የሚነሱ መሆኑን በመጥቀስ ዩኒቨርሲቲው ዘርፉን መፈተሸ ያለበት መሆኑን፣ የትራንስፖርት ችግርን ያለውን ሪሶርስ በአግባቡ በመጠቀም መፍታት እንደሚገባ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለሀገርና ለተቋሙ ፋይዳ በሌላቸውና ገጽታ ለሚያበላሹ ጉዳዮች ከመጠቀም ይልቅ ማኅበረሰቡን ዓለም ለደረሰበት ደረጃ የሚያበቁ ሀሳቦችን ለማካፈል መገልገል ይገባል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ለምርምርና ለሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ቦታዎችን እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ ብርሃኑ ቦታዎቹ ግን ምንም ሳይሠራባቸው መቀመጥ እንደሌለባቸው አሳስበው ዩኒቨርሲቲው በውሃ ምርምርና በሌሎችም የልኅቀት መስኮች ልቆ እንዲወጣ ለማድረግ ሁሉም በንቃትና በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ከበደ ግዛው እንደ ሀገር የትምህርት ዕድልን አስመልክቶ 3ኛ ዲግሪ 14%፣ 2ኛ ዲግሪ 67% እና የመጀመሪያ ዲግሪ 19% የደረሰ በመሆኑ በቀጣይ የትምህርት ትኩረት አቅጣጫ የሚሆነው 2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ላይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር ለመምህራን የውጪ ትምህርት ዕድል እያመቻቸ ቢሆንም ካለንበት ሀገራዊ ሁኔታ አንጻር በተለያዩ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች አድሚሽን ላገኙ መምህራን እንደየ አስፈላጊነቱ እየታየ የትምህርት ዕድልና ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች በምደባ ሳይሆን በፍላጎት ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲመጡ የሚያበረታቱ የስበት ሥራዎችን መሥራት፤ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ በምርምር ላይ ትኩረት በማድረግ ከመሠረታዊ ምርምር ወደ ተግባራዊ ምርምር በመግባት የምርምር ሥራዎችን መሥራትና የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ እንደ እንሰት ፕሮጀክት ያሉ ምርምሮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ እንዲሁም በብሔርና በሐይማኖት ጥላ ስር በመደበቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ድብቅ አጀንዳ የሚያራምዱ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው መቆጠብ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ አክለውም በተነሱት ተግዳሮቶች ላይ ሁሉም የድርሻውን መውሰድ ያለበት ሲሆን አፈጻጸሙም በቀጣይ የሚገመገም ይሆናል፡፡ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ሀገራችንን ከፍ የሚያደርግ ሥራ መሥራት አለብን ያሉት ዶ/ር ሹመቴ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ባለሙያዎች ምደባን አስመልክቶ የተነሱ ቅሬታዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ እንዲሁም በአንዳንድ ኃላፊዎች መካከል ያሉ ያለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ሹመቴ በአጠቃላይ ቦርዱ በተሰጠው ሥልጣን ልክ የሚሠራ መሆኑን ገልጸው በዩኒቨርሲቲው በኩል የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናቀቅ፣ ተባብሮ በመሥራትና በመቀራረብ ችግሮችን መፍታትና የፍቅር፣ የአንድነትና የውጤት ምክንያቶች መሆን አለብን ብለዋል፡፡

ውይይቱ በሦስት ዙሮች የተካሄደ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሹመቴ ግዛው፣ ም/ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴና የቦርድ አባል አቶ ከበደ ግዛው እንዲሁም የካውንስል አባላት፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት