Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል የፍትሕ እና የሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ የሕግ ት/ቤቶች ማኅበር ጋር በመተባበር ‹‹Contemporary Challenges, Trends and Governance of Internally Displaced Persons Protection in Ethiopia›› በሚል ርዕስ 2ኛውን ዓመታዊ የምርምር ጉባዔ አካሂዷል፡፡ በጉባዔው ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት በመጡ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የፌዴራል የፍትሕ እና የሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት የጥናትና ምርምር ዘርፍ ም/ዋ/ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ እንደገለጹት በሀገራችን በሪፎርም ላይ ብትሆንም ግጭት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ አንበጣ፣ የእርስ በእርስ ጦርነትና ሌሎችም ተግዳሮቶች የዜጎች መፈናቀልን አስከትለዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በርካታ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያስተናገደች ሲሆን ተፈናቃዮቹ ለከፋ ችግር ተዳርገዋል፤ ሰብዓዊ መብታቸውም ተደፍሯል፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በአሁናዊ የማኅበረሰብ ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በመፍትሔ ሃሳቦች ዙሪያ በጋራ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል እንደተናገሩት ተቋማቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃይን የሚመለከት ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት በማቋቋም በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላይ በሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ተያያዥ ችግሮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን መጎብኘታቸውንና አስፈላጊውን እገዛ እያደረጉ እንደሆነም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ምዕራብ ኬንያን ጨምሮ በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ፣ ሶማሌና ኦሮሚያ የተከሰተው ድርቅ የዜጎችን መፈናቀል በማስከተሉ በአካባቢዎቹ ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የፌዴራል የፍትሕ እና የሕግ ምርምር ሥልጠና ኢንስቲትዩት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ዘካሪያስ ኢርኮላ በበኩላቸው በዓውደ ጥናቱ ከዜጎች መብት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ገንቢ ሃሳቦች ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው አካላት መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ላለፉት 3 ዓመታት በሀገራችን በሕዝቡ ዘንድ ተስፋ የተጣለባቸው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት፣ ዘላቂ መረጋጋትና ሰላም ለማስፈን እንዲሁም ፖለቲካዊ ምኅዳሩን ለማስፋት የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዘካሪያስ በመድረኩ ላይ የተሳተፉም ሆነ ሌሎች ምሁራን በሀገራችን ምሁራን መካከል የሚታየው ልዩነት እንዲቀረፍና ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ከሲምፖዚየሙ የሚገኙ የምርምር ሃሳቦች በወቅታዊ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረጉ በመሆናቸው የሚሰጡ ሃሳቦችን መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት የመፍትሄ አካል አድርገው ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ የተጣለበትን የምርምር ተልዕኮ ለመወጣት ለመንግሥት ፖሊሲ፣ ለአስተዳደርና ለአመራር የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ለማቅረብ በነባራዊና ሀገራዊ ችግሮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች

የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በቀጣይም ለሰላም ዘብ በመቆም የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው እስኪመለሱ የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተ/ፕ በኃይሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት የቀድሞ ዲንና መምህር አቶ ደርሶልኝ የኔአባት በበኩላቸው ምርምሮችን መሥራት፣ ውይይቶችን ማካሄድና ሀገራዊ ችግሮች ለዘለቄታው እንዲፈቱ ምክክር ማድረግ ከዩኒቨርሲቲ ዓላማዎች ውስጥ የሚካተቱ መሆኑን ጠቅሰው ዓላማዎቹን መሠረት በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ከፌዴራል የፍትሕ እና የሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ ሕግ ት/ቤቶች ማኅበር ጋር በመቀናጀት የምርምር ጽሑፎችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ጉባዔው መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሐይማኖት ተቋማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተመራማሪዎች የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን ከየተቋሞቻቸው አንፃር የሚፈትሹበትና ግዴታዎቻቸውን የሚወጡበት ነው ብለዋል፡፡

‹‹Displacement, Transitional Justice and Reconciliation; Rejuvenating the Role of Reconciliation Commission››፣ ‹‹Conflicts and Forced Internal Displacement An Overview of Internally Displaced Peoples Security Crisis and Trends in Ethiopia››፣ ‹‹Administrative Restructuring Triggered Conflicts and IDPS in the Disintegrated Segen Area people zone››፣ ‹‹The Responsibility to Prevent Internal Displacement; in the Context of the Rights of Regional Minorities; The case of Ethiopia›› ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት