Print

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር 28ኛው ሀገር አቀፍ ኮንፍራንስ ላይ ከቀረቡ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቅ ሀና እንዳሻውና በማስተርስ ዲግሪ ምሩቅ ሁሴን አሊ የላቀ የመመረቂያ ጽሑፍ በማቅረብ ታኅሣሥ 9/2014 ዓ/ም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር በየዓመቱ ኮንፍራንስ ሲያዘጋጅ ለሀገር ፖሊሲ የሚጠቅሙና ትልቅ ፋይዳ ያላቸው የምርምር ውጤቶች ቀርበው ከአባላቱ ጋር ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን የተሻለ ምርምር ለሠሩ ባለሙያዎች የማበረታቻ ሽልማት ይበረከታል፡፡

በዘንድሮው ውድድር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ተሸላሚዎችን ማግኘቱ ለዩኒቨርሲቲው ገፅታ ግንባታና በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች የሞራል ስንቅ መሆኑን ዶ/ር መስፍን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የማኅበሩን ተደራሽነትን ከፍ ለማድረግ አርባ ምንጭ ላይ የማስተባበሪያ ቢሮ የሚከፈት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር መስፍን የማስተባበሪያ ቢሮው መከፈት ለዩኒቨርሲቲው፣ ለአካባቢውና ለክልሉ የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት