Print

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴርና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ‹‹ኑ የፈረሰውን የትውልድ ማፍሪያ ተቋም እንገንባ›› በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲ ሕዝብ ግንኙነት ም/ፕሬዝደንት፣ ዳይሬክተሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ጥር 21/2014 ዓ/ም ውይይት አካሂደዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የሰው ልጅ ቀደምት መገኛና የሥልጣኔ መነሻ የሆነችው ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በውጭና በውስጥ ፀረ-ሠላም ኃይሎች በሚሠነዘርባት ጥቃት ማደግ የሚገባትን ያህል ማደግ አለመቻሏን ተናግረዋል። አሸባሪው የሕወኃት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በፈፀመው ወረራና ጥቃት በርካታ መሠረተ ልማቶች የፈረሱ መሆናቸውን የጠቆሙት ፕሬዝደንቱ ከነዚህ ተቋማት መካከል የትምህርት ተቋማት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል። አሁን ላይ በአሸባሪው ቡድን የፈረሱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ተማሪዎችን ወደ መደበኛ ተግባራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ዜጎች እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው የገለጹት ዶ/ር ዳምጠው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ከዚህ አንፃር የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር ከዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በአሸባሪው ቡድን የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በሚያስፈልገው የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች አፈፃፀምና ቀጣይ ዕቅድ ላይ የተደረገው ውይይት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሯ የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉ ከዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የዩኒቨርሲቲውንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማንቃትና የችግሩን ግዝፈት በማስገንዘብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ድጋፉ የተጎዱና የወደሙ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችንም ጭምር ያካተተ እንዲሆን ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ተማሪዎችን ወደ መደበኛ ትምህርታቸው ለመመለስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሯ ከዚህም አንፃር የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶች ተቀይሰው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በገቢ ማሰባሰብ ሥራዎችና ዘመቻዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ድጋፍ በመሰበሰብ ረገድ የሚጠበቅባቸውን አበርክቶ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ አመለወርቅ ህዝቅኤል በበኩለቸው በአሸባሪው የሕወኃት በድን ጠብ አጫሪነት ሳንፈልግ በገባንበት ጦርነት ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውሶችን የፈጠረ መሆኑን ተናግረው አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በዚሁ ቡድን ከፍተኛ የሆነ ወድመት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ እነዚህን የተጎዱና የወደሙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት አሁን ላይ ባለው ግምት ከ19 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መረጃዎች እንደሚያሳዩ የተናገሩት ዳይሬክተሯ ተቋማቱን መልሶ ለማቋቋም እንደ ሀገር እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባልም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በ3 ክላስተሮች ተከፍለው በጦርነቱ ለተጎዱና

ሙሉ በሙሉ ለወደሙ ዩኒቨርሲቲዎች የገንዘብ፣ የዓይነትና ሌሎች ድጋፎችን እያደረጉ ሲሆን የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ወሳኝ በመሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡

የውይይት መድረኩ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የከፍተኛ ትምህርትና የአጠቃላይ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ለማከናወን፣ በተቋማቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት በትክክል በመለየት የዩኒቨርሲቲዎች የቀድሞ ተማሪዎች ወይም አልሙኒዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ሌሎች ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተጎዱ ወይም ሙሉ በሙሉ የወደሙ ተቋማት ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ተደራጅቶ ለወጥ የመረጃ ፍሰት እንዲውል ብሎም ለዓለም ማኅበረሰብ በእንግሊዝኛና በሌሎች ቋንቋዎች ጭምር እየተሠራ ተደራሽ እየተደረገ በምዕራባውያንና ደጋፊዎቻቸው አመካኝነት በሀገራችን ላይ እየደረሰ ያለውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሲስተምስና ኮሚዩኒኬሽን ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ በተጎዳው አማራ ክልል የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በክልሉ የሚገኙ የ10 ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በማስተባበር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የአልባሳትና የምግብ እህል ድጋፎች በስፋት ሲያቀርብ መቆየቱን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም ለህልውና ዘመቻው ከወር ደምወዙ ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ ከገንዘብና ከቁሳቁስ ድጋፎች ባሻገር በተለያዩ ሙያዊ ዘርፎች ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ዶ/ር ዘውዱ ከዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል የተወጣጡ የህክምና ባለሙያዎች እስከ ጦር ግንባር ድረስ በመሄድ በሙያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የተደረገው የውይይት መድረክም በጦርነቱ የተጎዱ መሠረት ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም የጋራ ዕቅድ ይዞ በትብብር ለመሥራት ስለሚያግዝ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አስናቀ በበኩላቸው ወልድያ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ በእጅጉ ከተጎዱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረው በዚህም በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የመማሪያ፣ መመገቢያ፣ መኝታ፣ ቤተ-ሙከራ፣ ቤተ-መፃሕፍት፣ አስተዳደር ሕንፃዎች ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁሶች ተቋሙ አገልግሎት እንዳይሰጥ በሚያደርግ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ መዘረፋቸውንና ቀሪዎቹ መውደማቸውን ገልጸዋል፡፡ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲስተምን ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ነው ያሉት ኃላፊው ዩኒቨርሲቲውን መልሶ ለማቋቋምና ሥራ ለማስጀመር አ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ 9 ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴርም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖችና በጦርነቱ ምክንያት ለወደሙ ተቋማት ያደረጓቸውን የገንዘብ፣ የዓይነትና ሙያዊ ድጋፎች በሪፖርት መልክ ያቀረቡ ሲሆን ችግሩ ሙሉ በሙሉ እስከሚቀረፍ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በቅንጅት ለመሥራት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት