Print

በዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ከ13 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለተወጣጡ መምህራን ‹‹Solid work››፣ ‹‹Arc cad›› እና ‹‹Auto cad›› በተሰኙ የኮንስትራክሽን ሶፍትዌሮች ዙሪያ ከጥር 16-20/2014 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ሠልጣኞች በቴክኖሎጂ አቅማቸውን በመገንባትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ወደ ማኅበረሰቡ ማሸጋገር እንዲችሉ የተዘጋጀ ሥልጠና ነው፡፡ ከሥልጠናው በኋላ ሠልጣኞች የሚሠሩትን እንከታተላለን ያሉት ዶ/ር ቶሌራ የሚሠሯቸውን ቴክኖሎጂዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን ለማኅበረሰቡ ለማድረስ በትብብር እንሠራለን ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ም/ዲን አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል በበኩላቸው ቴክኖሎጂ በአግባቡ ዲዛይን ካልተደረገና ዲዛይኑን ጠብቆ ካልተመረተ ለሚፈለገው አገልግሎት የማይውል ስለሆነ የሥልጠናው ዓላማ ይህንን የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ትስስሩ እያደገ የሚሄድ መሆኑንና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አንጻር ተቀራርቦ በመሥራት በኩል የተሻለ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና አሠልጣኝ አዳነ ካሳ ሠልጣኞች ሃሳባቸውን ወደ ወረቀት ለማዞር የሶፍትዌሮቹ ክሂሎት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በሶፍትዌሮቹ አጠቃቀም ዙሪያ ያገኙትን መሠረታዊ ዕውቀት በራሳቸው ማዳበር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል የአርባ ምንጭ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት መምህር ትዕግሥቱ ባዩ እንደተናገረው ለሥልጠናው የተሰጠው ጊዜ አጭር ቢሆንም ሥልጠናው በሶፍትዌሮቹ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለውን የክሂሎት ክፍተት ለመቅረፍ ጉልህ ሚና ስለሚኖረው መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

በሥልጠናው መጨረሻ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት