Print

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ጋር በመተባበር በፍትሐብሔር አሠራር ማኑዋል፣ በግንባታ ውሎች፣ በፍርድ ቤት ሥልጣን፣ በክስ አቀራረብና መስማት ሂደት እና በመጥሪያ አደራረስ ላይ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ ዐቃቤያን ሕግ ከጥር 28-29/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሶፎንያስ ደስታ በንግግራቸው ላለፉት 4 ዓመታት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸው የተለያዩ ግንዛቤዎችን ለማዳበር ሥልጠና አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት ፍትሕ ለአንድ አገር እድገት ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ኅብረተሰቡ የደረሰበትንና ወደ ፊት ሊደርስበት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ የኑሮ እድገት ደረጃን ያንፀባርቃል፡፡ ስለሆነም የፍትሕ ይዘትና ጥራት፣ አደረጃጀት፣ አወቃቀርና አመቺነት፣ የፍትሕ መተግበሪያ ዘዴ እንዲሁም አጠቃላይ ሥርዓተ ፍትሕ ግልፅና በተገቢው መንገድ የሚመራ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት በፍትሕ ዘርፍ የተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ይሠራል ያሉት ዶ/ር ተክሉ በተለይ ለሴቶች፣ ለሕፃናትና ለአቅመ ደካሞች ነፃ የሕግ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ ሥራውን በሚያሳልጡ ማዕከላት የክስ አቤቱታ፣ ጥብቅና፣ ሙያዊና ቁሳዊ ድጋፎች እንዲሁም ‹‹የሕግ መንገድ›› የተሰኘ ግንዛቤ ማስጨበጫ የሬዲዮ ፕሮግራም እንደሚዘጋጅም ተናግረዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት መምህርና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ሱራፌል ደመላሽ ዐቃቤያን ሕግ በፍትሐብሔር ጉዳይ ላይ ሲሠሩ ዋና ሥራቸው የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም ማስጠበቅ ስለሆነ በተለያየ መንገድ የሕዝብና የመንግሥት ጥቅም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የፍትሕ ሥርዓቱ ጋር በጣምራ እንዲሠሩ ግንዛቤን ማስጨበጥ የሥልጠናው ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ት/ቤቱ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስተባባሪው ጠቅሰው ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ጋር በትብብር ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ሥልጠናው ያካተታቸው ርዕሰ ጉዳዮች ወቅታዊና የዘርፉን ባለሙያዎች ግንዛቤ በማሻሻል ለማብቃት እንደሚያስችሉ ተናግረው ከዩኒቨርሲቲውና ከክልሉ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ጋር ያለው ትስስር አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ መጨረሻ ከሠልጣኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡