Print

ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለተወጣጡ አካዳሚክ አመራር አካላትና መምህራን ‹‹Academic Program Audit››፣ ‹‹Academic Program Standardization›› እና ‹‹Academic Program Accreditation›› በሚሉ ይዘቶች በትምህርት ፕሮግራም ጥራትና አግባብነት ዙሪያ ከየካቲት 21-22/2014 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው በተለይ ላለፉት 15 ዓመታት የከፍተኛ ትምህርትን ለማስፋፋት የመንግሥትና የግል ተቋማት በርካታ ሥራዎችን በመሥራታቸው ተደራሽነቱ የተሳካ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ወደ ትምህርት ጥራት ዞረናል ብለዋል፡፡

በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ መሠረት ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የጠቀሱት ዶ/ር ዳምጠው ይህንን ለማሳካት የመምህራን ሚና ትልቁን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት መስክ ብቁ ከሆኑ መሠረተ ልማት ባልተመቻቸበት ሁኔታም ቢሆን ተማሪዎቻቸውን ውጤታማ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎቻችን በገበያ ተቀባይነት እንዲኖራቸው የትምህርት ፕሮግራሞች አግባብነት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው ገልጸዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ለአገር እድገት ቁልፍ ሚና ያለውን ዕውቀት ለማስፋፋት ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣትና ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ፣ የኮሌጅና የት/ክፍል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ መምህር የሕልውና ጉዳይ የሆነውን ትምህርት በአስተማማኝ መሠረት ላይ በመገንባት ጥራቱን ለማስጠበቅ የትምህርት ፕሮግራሞች ኦዲትና አክሪዲቴሽን በመሥራት ክፍተቶችን ለይቶ ማስተካከል እንደሚገባ ዶ/ር ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የትምህርት ጥራት ኦዲትና ማጎልበት ባለሙያ አቶ ሲሳይ ተክሌ እንደገለጹት የአካዳሚክ ፕሮግራም ኦዲት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጧቸው አካዳሚክ ፕሮግራሞች ያሉባቸውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች የሚገመግሙበትን መሠረታዊ ነገር የሚያስጨብጥ ነው፡፡ ሥልጠናው የአካዳሚክ አመራሮችና መምህራን በዩኒቨርሲቲያቸው፣ በኮሌጃቸውና በት/ክፍላቸው ያለውን ፕሮግራም በመገምገም ያሉባቸውን ክፍተቶች በአጭርና በረጅም ጊዜ ለመሙላትና ለማሻሻል አቅም የሚፈጥርላቸው ነውም ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህርና የሥልጠናው ተሳታፊ ዶ/ር መለሰ መንገሻ በአስተያየታቸው ሥልጠናው በእጅጉ ጠቃሚ ቢሆንም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከታችኛው ደረጃ ጀምሮ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ደረጀ እንግዳው፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ንጉሴ ጋቢዩ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራት ኦዲትና ማጎልበት ባለሙያዎች፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዝደንቶች፣ የ2ቱ ኢንስቲትዩቶች ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮችና የኮሌጅ ዲኖች፣ የት/ክፍሎች የሥራ ኃላፊዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት