Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር 126ኛውን የዓድዋ ድል ክብረ በዓል ‹‹ዓድዋ ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት ለአፍሪካዊያን የነፃነት ጮራ›› በሚል መሪ ቃል የካቲት 23/2014 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው በደማቅ ሁኔታ አክብሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ አፍሪካ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ በወደቀችበት ዘመን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆችዋ ተጋድሎ ነፃነትዋንና ሉዓላዊነትዋን አስከብራ የኖረች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዓድዋ ድል ጀግኖች አንድነታቸውንና ዕሴቶቻቸውን ጠብቀው፣ በቋንቋና በብሔር ሳይከፋፈሉ የአንድነታቸውን ምንጭ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያሳዩበት ነው ያሉት አቶ ኃይለማርያም የዓድዋ ድል የአንድነታችን መገለጫ እንጂ ልዩነትን የማያመጣ መሆኑን በመገንዘብ ሁላችንም ሰላማዊ፣ የበለጸገችና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት መትጋት አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ባስተላለፉት መልዕክት የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን፣ ለአፍሪካዊያንና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት እንዲሁም በነጮች የዘር የበላይነት ጫና ስር ለነበሩ ጥቁር ሕዝቦችና በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ የማንቂያ ደወል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዓድዋ ድል የጥንት አባቶቻችን ለሀገር ያላቸውን ፍቅርና አንድነት የገለጹበት ትልቅ ድል ነው ያሉት ዶ/ር ዳምጠው የአሁኑ ትውልድም የአባቶቻችንን ፈለግ በመከተል ለሀገራችን አንድነትና ሉዓላዊነት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው ዓድዋ የቀደሙት አባት አርበኞች በዓል ብቻ ሳይሆን ትውልድ ታሪክን እየዘከረ የሚኖርበት ድል መሆኑን ገልጸው የዓድዋ ድል መዘከሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለቀጣይ ትውልድ ታሪክ አስቀምጦ እንዲያልፍ የሞራል ስንቅ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ተወካይ አርበኛ አቶ ጌታቸው ዓለማየሁ የአሁኑ ትውልድ እንደ አባቶቻችንና እናቶቻችን በአንድነትና በመቻቻል ለሕዝቦች ደኅንነት፣ ለሀገር አንድነትና ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ፕ/ር ሹመት ሲሻኝ በዓድዋ ድል ታሪካዊ እውነታዎችና ተሞክሮዎች ላይ ሰፊ ሙያዊ ትንታኔ አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ማርቺንግ ባንድ በአርባ ምንጭ ከተማና በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ የማርሽ ትዕይንት ያሳየ ሲሆን በዓሉን የተመለከቱ የተለያዩ ሙዚቃዊ ድራማዎች፣ መነባንብና ተውኔቶች፣ በዓድዋ ጦርነትና ድል ላይ ያተኮሩ ቁልፍ መልክቶችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነዶች ቀርበዋል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግሥት፣ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የክልሉ ፖሊስ ማርቺንግ ባንድ፣ የጋሞ ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት፣ የጋሞ አባቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመምህራንና የተማሪዎች ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ ተሳታፊዎች በፕሮግራሙ ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት