Print

‹‹የምኅንድስናና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለዘላቂ ልማት እና ተግዳሮቶች/3rd National Conference on Innovation and Challenges in Engineering and Technology for Sustainable Development›› በሚል ርዕስ 3ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ከግንቦት 26 - 27/2014 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስፋፋትና ተደራሽነትን በማሳደግ ለሁሉም ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት መሥራት የሚጠበቅባቸው ሲሆን በዘርፉ ዕውቀትን ማመንጨት፣ ክሂሎትን ማዳበርና በምርምር አማካኝነት ቴክኖሎጂን ማሸጋገር ለኢንደስትሪ ዕድገትና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ መሰል ተግባራትን በማከናወን ለሀገር ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በጋሞ ዞን የሚገኙ የገጠር ጤና ጣቢያዎችንና ትምህርት ቤቶችን ከፀሐይ ብርሃን በሚገኝ ታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ሥራዎች መከናወናቸው ለአብነት እንደሚጠቀሱ የተናገሩት ፕሬዝደንቱ በቀጣይ በሌሎችም መስኮች አገልግሎቱ በጥራትና በሽፋን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ በማድረግ የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማስፋት ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው እንደተናገሩት ዓውደ ጥናቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ማኅበረሰቡን ለመጥቀም የተሠሩ የምኅንድስና እና የቴክኖሎጂ ምርምር ሥራዎች የሚቀርቡበት ነው፡፡ ዶ/ር ሙሉነህ በባዮ ጋዝ ዘርፍ ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመሆን 250 የቤት እመቤቶችን ተረፈ ምርትን በመጠቀም የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከክርስትያን ኤይድ ጋር በመተባበር መብራት በማይደርስባቸው የገጠር አካባቢዎች አነስተኛ ግድብ በመሥራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑ እንዲሁም በዞኑ ገጠር ቀበሌያት ውስጥ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ትምህርት ቤቶች ከፀሐይ ብርሃን በሚገኝ ታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ ሥራዎችና ሌሎችም መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነህ በተጨማሪም በዓውደ ጥናቱ የቀረቡ የምርምር ሥራዎች በኤሌክትሪካልና ሜካኒካል፣ በኮምፒውቲንግና ሶፍትዌር፣ በሲቭል ምኅንድስና እና በሕንፃ ግንባታ ጥራትና ውበት ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው መድረኩ ተመራማሪዎች እርስ በእርስ የሚማማሩበትና በቀረቡ የምርምር ሥራዎች ላይ ሙያዊ አስተያየቶች የሚሰበሰቡበት ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሜካኒካልና ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ ኢንስቲትዩት የመጡት ፕሮፈሰር ዳንኤል ቅጣው እንደገለፁት በሀገራችን የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ውጤቶችን ለማኅበረሰቡ የማድረስ ሥራዎችን እየሠሩ እንዳለ ቢታወቅም በሌላኛው ጎን ደግሞ በበርካታ ምሁራን የተሠሩ ምርምሮችና ጥናታዊ ጽሑፎች የታለመላቸውን ዓላማ ከማሳካት አንፃር ሲታይ ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡ የአንድ ሀገር ዕድገት የሚለካው በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት በመሆኑ እንደ ሀገር ከሌላው ዓለም ጋር ለመወዳደር የሚያስችል

የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ማምጣት እንደሚጠበቅና ይህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና መሆኑን ፕሮፌሰር ዳንኤል አስምረዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ አክለውም የልቦና ውቅርን በማስተካከል የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ማረጋገጥ በዘርፉ የሚታየውን ተግዳሮት ለመቀየርና ለዕድገት ዝግጁ እንደሚያደርግ ጠቅሰው ሳይንስ ከሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ጋር እንዲዋሃድ ሲደረግ በኅበረተሰቡ ዘንድ በቀላሉ ግንዛቤ መፍጠርና ማስረጽ ብሎም ወደ ተግባር የመለወጥ ዕድሉ ሰፊ ይሆናል ብለዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከ13 ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተመራማሪዎች የተለያዩ ጥናቶችን ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ረዳት ፕሮፌሰር ምንይችል አለኸኝ በኮቪድ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ላይ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ማሽን ሰውን ተክቶና ከሰው ንክክ ውጭ ሆኖ በመሥራት በመጪ ጊዜ የሚከሰተውን የኮቪድ ጉዳት አስቀድሞ መተንበይ እንደሚያስቸል “Prediction of COVID – 19 Using Deep Learning Approach” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ አስረድተዋል፡፡

ሌላኛውን ጥናታዊ ጽሑፍ “Design a Unique-ID Based Cyber defense framework or Enhancing Security of Ethiopian Social Media Use, in Case of Facebook” በሚል ርዕስ ያቀረቡት የአርባ ምንም ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውቲንግና ሶፍትዌር ምኅንድስና ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ባሻ ቃሲም በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ሊስተካከሉ በሚገቡ ማነቆዎች ላይ ያተኮረ ጥናት ማካሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡ ተመራማሪው በተለይ በሀገር ደረጃ ሶሻል(መኅበራዊ) ሚዲያ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በተለይ በፌስቡክ (Facebook) አንድ ግለሰብ ከአንድ በላይ አካውንት በመክፈት በሐሰተኛ አካውንቶች የሌሎችን ስምና የሰው ስም ያልሆኑ መጠሪያዎችን በመጠቀም በድብቅ የተለያዩ አጀንዳዎችን ይዘው ቀውስ የሚያስከትሉና ተጽዕኖ ፈጣሪ መልዕክቶችን በማሠራጨት ላይ የሚሠሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ተመራማሪው የሐሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት መቆጣጠር አንዱ የማኅበረሰብ ደኅንነት አካል እንደመሆኑና ዜጎችም እውነተኛ መረጃ ብቻ ተዳራሽ እንዲሆንላቸው ስለሚገባ ሐሰተኛ መረጃዎችን በቀላሉ መቅረፍ የሚችል ሶፍትዌር መፍጠራቸውንና ይህም አንድ ተጠቃሚ ከአንድ በላይ የፌስቡክ አካውንት በመክፈት መጠቀም እንዳይችል እንዲሁም በመታወቂያው ላይ ባለ መረጃ ወይም ቀድሞ በተሞላው መረጃ መሠረት ተመሳሳይ ወይም ሐሰተኛ አካውንት እንዳይከፈት በማድረግ የሐሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሜካኒካልና ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ ኢንስቲትዩት የመጡት ፕሮፈሰር ዳንኤል ቅጣው፣ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪካል ኢንጂነርስ ሶሳይቲ የመጡት ዶ/ር ኢንጅነር ብርሃኑ ግዛው፣ ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የመጡት ካፒቴን ጌትነት ዓባይ፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ፣ ከኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች የመጡ እንግዶችና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከ13 ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ምሁራን 18 የምርምር ጥናቶችና 3 የፖስተር ገለጻ ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት