Print

የኢትዮጵያ ሁዋዌ አይ.ሲ.ቲ አካዳሚ/Huawei ICT Academy/ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ (ICT) እና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬቶች ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች ስለ ሁዋዌ አይ.ሲ.ቲ ታለንት ኢኮሲስተም /ICT Talent Ecosystem/ ግንቦት 24/2014 ዓ.ም ገለጻ/ ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢትዮጵያ ሁዋዌ አይ.ሲቲ አካዳሚ የICT ኢኮሲስተም ዴቨሎፕመንት ማኔጀር አቶ ታምሬ ዳውድ እንደተናገሩት የገለጻው ዓላማ የኦንላይን ሥልጠና የሚሰጥበት የሁዋዌ አይ.ሲ.ቲ አካዳሚ ማዕከል/Huawei ICT Academy Center/ በመክፈት ተማሪዎች በተለይ ከአይ.ሲ.ቲ/ICT/ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጋር ጠንካራ ግኝኙነት እንዲኖራቸውና ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ወደ ቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሙያ ዘርፎች እንዲቀላቀሉ ለማስቻል ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በዓመታዊ የአይ.ሲ.ቲ ውድድር ላይ ተማሪዎች የፈጠራ ሥራቸውን በማቅረብ እንዲወዳደሩ ማድረግ እና ተማሪዎች ሀገራቸውን ወክለው ወደ ቻይና ሀገር በመሄድ የባህልና የቴክኖሎጂ ልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ድርጅቱ በሚሰጣቸው ዕድሎች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ታምሬ ሁዋዌ በቅርቡ በፎሩቹን ጋዜጣ የወጣውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ድርጅቱ በሀብት ሠንጠረዥ በዓለም 44ኛ ደረጃ፣ በቴሌኮም ቴክኖሎጂ ቀዳሚ እና በአፍሪካ ከ140 በላይ ሀገራት የሁዋዌ የቴሌኮም ግብዓት ምርቶችን ተጠቃሚ መሆናቸው በዘርፉ የበቁ ሠራተኞችን ለማብዛት መሰል የሥልጠና አማራጮችን ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ድርጅቱ በዓለም ከ200 ሺህ በላይ በአፍሪካ ደግሞ ወደ 86 ሺ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ከነዚያም ውስጥ 76ቱ ፐርሰንት የሚሆኑት የየአካባቢው ተወላጆች መሆናቸውን አቶ ታምሬ ተናግረዋል፡፡

ሁዋዌ ተማሪዎች በኦንላይን ፕላትፎርም ሲማሩ በሦስት ዓይነት መንገድ የምስክር ወረቀት የሚሰጥ ሲሆን “HCIA-Huawei Certified ICT Associate”፣ “HCIP - Huawei Certified ICT Professional” እና “HCIE - Huawei Certified ICT Expert” ይገኙበታል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ ሁዋዌ አካዳሚ ባለፈው ዓመት ባዘጋጀው ዓመታዊ የአይ.ሲ.ቲ ውድድር ላይ የተወሰኑ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በICT ዘርፍ ባቀረቧቸው የፈጠራ ውጤቶች የተወዳደሩ ሲሆን በዚህም ዩኒቨርሲቲው 2ኛ ደረጃ በመውጣት የምስክር ወረቀት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ ሁዋዌ አካዳሚ የሚሰጣቸውን የተሻሉ የኦንላይን ሥልጠናዎችን አግኝተው ሳይሆን ለቴክኖሎጂው ባላቸው ቅርበት በግላቸው ባደረጉት ጥረት ብቻ ተወዳድረው ማሸነፋቸውን ጠቁመው በተሻለ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራ ለዩኒቨርሲቲው ምሩቃን የተሻለ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም በሀገራችን አዳዲስ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ብቅ ብቅ እያሉ ስለሆነ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ዕድሎችን ለመጠቀም ዩኒቨርሲቲው ከድርጅቱ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችሉ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በሶፍትዌር፣ በሀርድዌር፣ በኤሌክትሪካልና በሲቪል ምኅንድስና ዘርፎች ያሉ ተማሪዎች ከቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር ተቀጥሮ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን ከዩኒቨርሲቲው የመረጃና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት አስፈላጊውን ትብብር እያገኙ የሥልጠናና የብቃት ማረጋገጫ ፈታና ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

አቶ መኳንንት ኃ/ሚካኤል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአይ.ሲ.ቲ ነባር ሲስተም አስተዳዳሪና የሁዋዌ አካዳሚ አስተባባሪ የሁዋዌን አገልግሎት አስመልክተው እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ሁዋዌ አካዳሚ በሀገራችን በICT፣ ሶፍትዌርና ሀርድዌር እንዲሁም በኤሌትሪካል ምኅንድስና ዘርፍ ያሉ ተማሪዎችን በማሠልጠንና ዕውቅና በመስጠት በቴክኖሎጂው ውጤታማና ብቁ እንዲሆኑ እያመቻቸ ቆይቷል፡፡ ተማሪዎች ትምህርቱን በነጻ እንዲያገኙ ለአስተባባሪዎቻቸው መጠነኛ ክፍያ በመፈጸም ድጋፍ እንደሚያደርግና ጠቅሰው አቶ መኳንንት ተማሪዎች በተዘጋጀው ፕላትፎርም በመመዝገብና በመማር የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፕሮግራሙ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት