Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ-ምረቃ ት/ቤት አስተባባሪነት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለተመረቁ መምህራን 3ኛው የእንኳን ደኅና መጣችሁ ‹‹የዶክተሮች ቀን/Doctoral Day›› መርሃ-ግብር ግንቦት 30/2014 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት 2ኛው ‹‹የዶክተሮች ቀን›› ከተከበረ ወዲህ 19 የዩኒቨርሲቲው መምህራን የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰዋል፡፡ ተመራቂዎቹን እንኳን ደኅና መጣችሁ ለማለት፣ በትምህርት ላይ ባሉበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲውን ድጋፍ ለመገምገም እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ለሚማሩ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ልምድ ለማካፈል ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ የሚከበረው ‹‹የዶክተሮች ቀን›› በዩኒቨርሲቲውና በኮሌጆች፣ በኢንስቲትዩቶችና በት/ቤቶች ደረጃ የምርምር አካባቢን ከማሳደግ አኳያ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ይህም እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ የመምህራንን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል፣ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ለማስፋፋትና የምርምር ሥራዎችን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ቃላቸውን ጠብቀው ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የተመለሱ መምህራን ላስመዘገቡት ስኬት ዕውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ መምህራኑ በሁሉም መስክ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚሰጥም ነው፡፡ ባደጉት ሀገራት ጭምር በየደረጃው የትምህርት ተግዳሮቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ዓለማየሁ ችግሮችን ለማሸነፍ ከጅምሩ ጥንቃቄ ማቀድና ራሳችንን ካለው ግብዓትና ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማስማማት ይገባል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ በቁርጠኝነትና በትጋት ሙያዊ አገልግሎታቸውን እንዲያበረክቱና እንዲሁም ተማሪዎቻቸውንና ማኅበረሰቡን በሙሉ አቅማቸው እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ በድኅረ ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ ኡንቻ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች አጠቃላይ ይዘትና አፈፃፀም ላይ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በት/ቤቱ የሚሰጡ የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በተመለከተ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ውስንነቶች በሪፖርቱ ተዳስሰዋል፡፡ መሰል መድረኮች የድኅረ ምረቃ ት/ቤት የአሠራር ሥርዓት ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን ለሚደረገው ጥረት ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችንና የተሻሉ ልምዶችን ለማግኘት እንደሚረዳ ዶ/ር አበራ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም መርሃ ግብሩን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በምርምር አፈፃፀም፣ በመማር ማስተማር፣ በአስተዳደራዊ አገልግሎት አሰጣጥና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ዶክተሮቹ በመማር ማስተማር ሂደት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፈው ለውጤት መብቃታቸው አስደሳች መሆኑንና በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በጋራ በመመካከር በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችንና ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ በዩኒቨርሲቲው በማስተማር ላይ የሚገኙ ዶክተሮችና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡