Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተቋማዊ ጥራት ግምገማ ወርክሾፕ ሰኔ 16/2014 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ በዕለቱ በኮሌጁ በሚገኙ የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ሲካሄድ የቆየው የውስጥ ኦዲት ግምገማ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

የኮሌጁ ቺፍ አካዳሚክ ዳይሬክተርና የቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተክሉ ተሾመ እንደተናገሩት ኮሌጁ ከትምህርት ጥራት አኳያ የትምህርት ፕሮግራሞችን በውስጥና በውጭ ገምጋሚዎች ኦዲት በማስደረግ ዕውቅና /Accreditation/ እንዲያገኙ ለማስቻል እየሠራ ነው፡፡ ወርክሾፑ በኮሌጁ የትምህርት ፕሮግራሞች የውስጥ ግምገማ ሪፖርት ላይ ውይይት በማድረግ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና ደካማ ጎኖችን በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ በተዋረድ እንዲፈቱ ለማስቻል እንዲሁም በት/ክፍሎች መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን አቶ ተክሉ ጠቁመዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የውስጥ ግምገማው የትምህርት ፕሮግራሞቻችን በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር የጎላ ሚና ይጫወታል ያሉት አቶ ተክሉ የግምገማ ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ከሥርዓተ ትምህርት መሻሻል፣ ከግብዓትና ከሰው ኃይል አቅርቦት አኳያ የሚሠሩ ሥራዎች በሁሉም ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የጤናና የሕክምና ባለሙያዎችን ለማፍራት ይረዳሉ ብለዋል፡፡

የፋርማሲ ትምህርት ፕሮግራምን ሪፖርት ያቀረቡት መ/ርት ቤተልሔም ሲራክ ት/ክፍሉ በ2010 ዓ/ም 26 ተማሪዎችን በመቀበል ሥራ እንደጀመረ አስታውሰው በፕሮግራም ግምገማው መሠረት ከ9ኙ የግምገማ መስፈርቶች አንፃር የፕሮግራሙ ሥርዓተ ትምህርት የተሻለ ነጥብ ማግኘቱንና በአንፃሩ በትምህርት ግብአት አቅርቦት ዝቅተኛ ነጥብ ያገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ መ/ርት ቤተልሔም በኮሌጁ ራሱን የቻለ የፋርማሲና የእንስሳት ቤተ-ሙከራ አለመኖር፣ የመምህራን፣ የማጣቀሻ መጻሕፍትና የቢሮ እጥረት ዋነኛ ውስንነቶች መሆናቸው በግምገማው የተረጋገጠ ሲሆን ችግሮቹን ለመቅረፍ ከት/ክፍል ጀምሮ በተዋረድ ያሉ አካላት በጋራ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የሕክምና ት/ቤትን ሪፖርት ያቀረቡት በት/ቤቱ የባዮሜዲካል ሳይንስ ት/ክፍል ኃላፊ ረ/ፕ አብነት ተሾመ በበኩላቸው በት/ቤቱ ብቁና ልምድ ያላቸው መምህራንና መሪዎች መኖራቸው፣ የተማሪዎች የምዘና ሥርዓት ኤሌክትሮኒክ መሆኑና ምዘናዎች በኦንላይን መሰጠታቸው እንደ ጠንካራ ጎን በግምገማው የተለዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ት/ቤቱ በበጀት ራሱን ችሎ እየሠራ አለመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲው የራሱ ሆስፒታል የሌለው መሆኑ፣ የቤተ-ሙከራ ግብዓትና የመምህራን ቢሮ እጥረት በግምገማው የተመለከቱ ውስንነቶች መሆናቸውን የገለጹት ረ/ፕሮፌሰሩ በትምህርት ጥራትና ብቁ ምሩቃንን በማፍራት ሂደት አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ውስንቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል ዕቅድ በት/ቤቱ የተዘጋጀ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለተግባራዊነቱ በትብብር እንዲሠሩ መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል፡፡

የውስጥ ግምገማው ፕሮግራሞቹን ከሥርዓተ-ትምህርት፣ የትምህርት ግብዓት፣ የምዘና ሥርዓት፣ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ፣ አስተዳደር፣ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎትና ሌሎች መለኪያዎች አንፃር የመዘነ ሲሆን በግምገማው የተመለከቱ ውስንነቶችን ለመቅረፍና ፕሮግራሞቹን ለውጭ ግምገማ ዝግጁ ሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውቅና ለማግኘት የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት