Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ከ ‹‹Social Sciences for Severe Stigmatizing Skin Conditions (5s Foundation) እና ከኢትዮጵያ ሶሲዮሎጂስቶች፣ ማኅበራዊ ሠራተኞችና አንትሮፖሎጂስቶች ማኅበር/‹‹Ethiopian Society of Sociologists, Social Workers and Anthropologists (ESSSWA) ጋር በመተባበር ከዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ከሰባቱም ት/ክፍሎች ለተወጣጡ 41 መምህራን ከሰኔ 16-18/2014 ዓ/ም በምርምር ሥነ ምግባር ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ተቋም እንደመሆኑ በምርምር ላይ ማተኮር እንዲሁም ልምዶችንና ሳይንሳዊ ግኝቶችን ከተለያዩ ተቋማት በመውሰድ የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ ሥራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምር ውጤቶች የሚታተሙባቸው ከሰባት የሚበልጡ ሳይንሳዊ የምርምር ጆርናሎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው ሥልጠናው ቀደም ሲል የነበረው የምርምር ሥራና የኅትመት ሁኔታ ከምርምር ሥነ ምግባር አኳያ የነበረበትን ደረጃና በቀጣይም እንዴት መከናወን እንዳለበት ጠቃሚ ግብዓቶች የሚገኙበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ ት/ክፍል መምህር፣ የ5S ፋውንዴሽን የምርምር ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪና የእለቱ የክብር እንግዳ ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ ጥራት ያለውና የተዋጣለት ምርምር ለመሥራት በተገቢ ሁኔታ የሠለጠኑ የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው ጥናትና ምርምር በማድረግ ሂደት ተመራማሪዎች በቅድሚያ የጥናትና ምርምር መርሆዎችን፣ ሕጎችንና ደንቦችን በሚገባ መረዳት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጌትነት በጥናትና ምርምር ሥነ ምግባር መርሆዎች ላይ የሚታዩ አከራካሪና አወዛጋቢ ሃሳቦችን በማንሳት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በማጠቃለያቸውም በተለይ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ለሚደረጉ ምርምሮች የምርምር ሥነ ምግባር መርሆዎች እንደየአካባቢው ሁኔታ የሚተረጎሙና የሚቀረጹ፣ የማኅበረሰቡን ሰፊ ተሳትፎ የሚጠይቁ፣ የተቋማዊ ግምገማ ቦርድን (IRB) የሚያሳድጉ መሆን እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሉ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ ‹‹ተቋማዊ የምርምር ሥነ ምግባር ጥራት ማረጋገጫ ገምጋሚ ቦርድ›› በኮሌጁ ለማቋቋም ግብዓት የሚሆኑ ሰዎችን ማፍራት፣ እንዲሁም በግላቸው የሚሠሯቸውን ምርምሮች የምርምር ሥነ ምግባር መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ እንዲያከናውኑ ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉ ሌሎች ኮሌጆችንም በማሠልጠን በዘርፉ ተጨማሪ የሰው ኃይል ማፍራትና በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የምርምር ሥነ ምግባርን የተከተሉ ሆነው እንዲሠሩ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ሥልጠናውን ከወሰዱ አባላት ውስጥ በማውጣጣት ገምጋሚ ቦርዱ እንደሚቋቋምና ይህም ጠቃሚ መሆኑን ዶ/ር እንዳልካቸው ገልጸዋል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት በዩኒቨርሲቲው የሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሶሲዮሎጂስቶች፣ ማኅበራዊ ሠራተኞችና አንትሮፖሎጂስቶች ማኅበር (ESSSWA) የደቡብ ምዕራብ ቻፕተር አስተባባሪ መ/ር አልአዛር ልሳኑ ተመራማሪዎች ምርምር በሚሠሩበት ወቅት የሚገጥሟቸውን ፈታኝ የሥነ ምግባር ጉዳዮች ተደራሽ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድና መሠረታዊ የሥነ ምግባር መርሆዎችን ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እንዴት ማገናዘብ እንደሚቻል በሰፊው ዳስሰዋል፡፡ መረጃ ከመሰብሰቡ በፊት ከመረጃ ሰጪው ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባ እንዲሁም የተገኙ መረጃዎች የመረጃ ሰጪዎችን የግል ሕይወትና ደኅንነታቸውን በማይጎዳ መልኩ በጥንቃቄና በምስጢር መቀመጥ እንዳለባቸው የተናገሩት መ/ር አልአዛር አንድ ጥናት ከመካሄዱ በፊት ንድፈ ሃሳቡ ቀርቦ የሥነ ምግባር መመሪያን የሚያሟላ መሆኑ ሊገመገም ይገባል ብለዋል፡፡

የጥናትና ምርምር መሠረታዊ ሕጎችና መንገዶችን እንዲሁም የምርምር ክፍተቶችን አስመልክቶ ሥልጠና የሰጡት የኮሌጁ ሶሲዮሎጂ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ባይሳ ፈዬ ሕፃናት፣ በአካል ጉዳትና በስነ ልቦና ችግር ውስጥ ያሉ እንዲሁም በሌላ አካል ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎችን የጥናታችን አካል አድርገን መረጃ እንዲሰጡን ከማድረጋችን በፊት ሕጋዊ ወኪሎቻቸውንና የመረጃ ሰጪዎቹን ፈቃደኝነት ልናገኝ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም መሠረታዊ ሕጎቹ በጥናትና ምርምር መመሪያ ውስጥ ገብተው ተቋሙ ሕጋዊ ዕውቅና ሰጥቶ ሊሠራበት፣ የጥናትና ምርምሩ ሂደትና ውጤት ቁጥጥር ሊደረግበትና ተቋሙም ከፍተኛ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ባይሳ አክለውም አጥኚዎች ጥናትና ምርምሮችን ሲሠሩ የሚኖረውን ውጣ ውረድ ተቋቁመው በመሥራትና ወደ ኅብረተሰቡ በማውረድ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም ተቋማት አደናቃፊ ጉዳዮችን እያስወገዱ የሥራ ስሜትን በማይጎዳ መልኩ መቆጣጠርና መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ምርምር በሚያደርጉበት ወቅት ሊከተሉ በሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች እና ተማሪዎችን በማማከር ሂደት ላይ ያላቸውን አስተውሎትና ዕውቀት የሚያዳብር እንዲሁም ያወቁትን በተግባር የሚያውሉበትን መንገድ የሚያስገነዝብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት