Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 3ኛውን ሀገራዊ ዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ፎረም ‹‹የቴክኖሎጂ ሽግግርና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርን ማሳደግ›› በሚል መሪ ቃል ሰኔ 21/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በሀገራችን ዘላቂ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራምን ተግባራዊ በማድረግና ወደ መካከለኛ ገቢ የሚደረገውን ጉዞ በማሳካት የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በመንግሥት የተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተነድፈው ሲተገበሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የልማት ግቦቹ ወደ ተግባር ተለውጠው የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማስፈፀም አቅም ግንባታ አለኝታ የሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከአስፈፃሚ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ ከኢንደስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች ጋር የሚኖራቸው የትብብር፣ የመደጋገፍና በጋራ የመሥራት ሚና ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው ጠቅሰዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥልጠና ጥራትን ለማስጠበቅና የንድፈ ሃሳብ ዕውቀቶችን ከተግባር ጋር ለማቆራኘት ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንደስትሪዎች ጋር የሚኖራቸው ትስስር በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ያወሱት ፕሬዝደንቱ በተመሳሳይም ኢንደስትሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች የሚፈልቁ አዳዲስ ዕውቀቶችን በመጠቀም የተሻለ ምርት በማምረት ትርፋማ እንዲሆኑ ትስስሩ የማይተካ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ስለ ቴክኖሎጂ ሲታሰብ የመጀመሪያ የሆነውና በ18ኛው መቶ ክ/ዘመን የጀመረው የኢንደስትሪ አብዮት ታሪካዊ ክስተት የማኅበረሰቡን ሕይወት ከግብርናና እጅ ሥራ ኢኮኖሚ ወደ ኢንደስትሪና ማሽን ማምረቻ የበላይነት የቀየረ ሂደት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ አዳዲስ የሥራና የአኗኗር መንገዶችን ለሰው ልጆች ከማስተዋወቃቸው ባሻገር የማኅበረሰቡን ሕይወት በመሠረታዊነት መለወጥ የቻሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂ ለእድገትና ልማት ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት ተ/ፕሮፌሰሩ ሀገራችን ቴክኖሎጂ የእድገቷ መሠረት እንደሆነ በመገንዘብ በምትንቀሳቀስበት በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርን ማጠናከርና የቴክኖሎጂ ፈጠራና ትውውቅ ሥራዎችን ማከናወን ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር፣ የማላማድ እንዲሁም ለሀገርና ለማኅበረሰብ ለውጥ እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ለመስኩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንና ባለፉት ጥቂት ዓመታትም አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራቸው ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የእንሰት አመራረትና ማብላላት ሂደትን ለማዘመን እየተሠሩ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንደ ማሳያ ይጠቀሳሉ ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ጅምር ሥራዎች የተሻለ ፍሬ አፍርተው ለማየት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚደረጉ መሰል የውይይት መድረኮች ጠቀሜታቸው የገዘፈ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲው ከ40 በላይ ኢንደስትሪዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በትብብር እየሠራ ሲሆን በየዓመቱ ከ4,000 በላይ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ከ50 በላይ መምህራን ወደ እነዚህ ኢንደስትሪዎች በመሄድ የተግባር ልምምድ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

ከፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር አንፃር ዩኒቨርሲቲው የበቆሎና የለውዝ መፈልፈያ፣ የወተት መናጫ እንዲሁም በኢኖቬቲቭ እንሰት ፕሮጀክት የተሠሩ የእንሰት ምርት ሂደት የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች ለማኅበረሰቡ ተሰራጭተው የማላመድ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር ቶሌራ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ከቀረቡ የምርምር ሥራዎች መካከል ‹‹Innovative Enset Processing Technologies, Value Added Products, Safe Storage and Longer Shelf Life›› በሚል ርዕስ በዶ/ር አሸናፊ አዛገ የቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው በባህላዊ መንገድ እንሰትን የማምረትና የማብላላት ሂዳት በእጅጉ አድካሚ ከመሆኑም ባሻገር 45 በመቶ የሚሆነው ምርት እንዲባክን ያደርጋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ምርምርን መሠረት ያደረጉ ቴክኖሎጂዎች ለማኅበረሰቡ እንዲሻገሩ ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

‹‹Potential Assessment of Coal Deposit in Gamo Zone, Kucha Woreda, Ethiopia›› በሚል ርዕስ በመ/ር ጎሳዬ ብርሃኑ የቀረበው ጥናት በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት የገንዘብ ድጋፍ በጋሞ ዞን ቁጫ ወረዳ የድንጋይ ከሰል ማዕድን አለኝታ ለማረጋገጥ የተካሄደ ጥናት ነው፡፡ የድንጋይ ከሰል ለሲሚንቶና ሌሎች ፋብሪካዎች በኃይል ምንጭነት የሚያገለግል ወሳኝ ማዕድን ሲሆን በተደረገው ጥናትም በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ 744,174.96/ ሰባት መቶ አርባ አራት ሺህ አንድ መቶ ሰባ አራት ከዘጠና ስድስት በመቶ/ ቶን የድንጋይ ከሰል መኖሩ እንደተረጋገጠ አቅራቢው ገልጸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሳታ ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ፣ ከቢሾፍቱ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩትና ከአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር መሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የተሠሩ ቴክኖሎጂዎች ጉብኝትም ተደርጓል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ የሰጠው ትኩረትና እየታዩ ያሉ ለውጦች አበረታች መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ የገለጹ ሲሆን ትስስሮችን ከማጠናከርና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ማኅበረሰቡ ከማዳረስ አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጅምር ሥራዎችን ማጠናከርና አዳዲስ ትስስሮች በመፍጠር መሥራት እንደሚገባ ከተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

በፎረሙ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሀብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ እና የቋሚ ኮሚቴው አባል ክቡር አቶ ፍሬው ተስፋዬን ጨምሮ ከተለያዩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ኢንደስትሪዎች፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከዞን ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት