Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለጂኦግራፊና አካባቢያዊ ጥናት ት/ክፍል መምህር ዶ/ር አበራ ኡንቻ እና ለውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህር ዶ/ር አክበር ጩፎ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል፡፡

በጋሞ ዞን ዲታ ወረዳ ዛላ ቀበሌ በ1965 ዓ/ም የተወለዱት ዶ/ር አበራ ኡንቻ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጎርቃ አባሳ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጨንቻ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ያጠናቀቁ ሲሆን በ1983 ዓ/ም ከባህር ዳር ፔዳጎጂካል ኮሌጅ በጂኦግራፊ ትምህርት ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል፡፡ በ1996 ዓ/ም በዲላ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ1999 ዓ/ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክ ጂኦግራፊ የማስተርስ ዲግሪ እንዲሁም በ2007 ዓ/ም በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ 3ኛ ዲግሪያቸውን አጠናቀዋል፡፡

ዶ/ር አበራ እስከ 2000 ዓ/ም በተለያዩ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶችና በአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በጂኦግራፊ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ በ2000 ዓ/ም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለው እስከ 2003 ዓ/ም በጂኦግራፊና አካባቢያዊ ጥናት ት/ክፍል ‹‹GIS››፣ ‹‹Economic Geography›› እና ‹‹Environment and Development Project Design›› ኮርሶችን ለመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች እንዲሁም እስከ 2006 ዓ/ም በ‹‹Advanced Research methods››፣ ‹‹Fundamentals of Remote Sensing›› እና ‹‹Seminar on Contemporary Geographic Issues›› ለተመራቂ ተማሪዎች ኮርሶችን ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር አበራ 10 አርቲክሎችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ያሳተሙ ሲሆን ከ30 በላይ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ዋና አማካሪና ለ2 የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ረዳት አማካሪ በመሆን ያስመረቁ ሲሆን ለ5 የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ረዳት አማካሪ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የጂኦግራፊና አካባቢያዊ ጥናት ት/ክፍል ኃላፊ፣ የኮሌጅ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች አስተባባሪ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ቢዝነስ እና ሶሻል ሳይንስ ጆርናል ኤዲተር ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር አንድ ግራንድ ፕሮጀክት በዋና አጥኚነትና 2 ግራንድ ፕሮጀክቶችን በረዳት አጥኚነት በመምራት ላይ ሲሆኑ በአንድ ቴማቲክ ምርምር በዋናነት እና በ2 ቴማቲክ ምርምሮች በቡድን አባልነት እየተሳተፉ ነው፡፡

ዶ/ር አክበር ጩፎ በወላይታ ሶዶ በ1977 ዓ/ም የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዋጃ ቄሮ እና ሶዶ ጊዮርጊስ ት/ቤቶች እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወላይታ ሶዶ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀው በ1998 ዓ/ም ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በ2001 ዓ/ም ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በኦርጋኒክ ኬሚስትሪ 2ኛ ዲግሪ እና በ2007 ዓ/ም ከ‹‹Beijing University of Chemical Technology›› በ‹‹Environmental Engineering›› 3ኛ ዲግሪያቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከ2009-2011 ዓ/ም በBeijing University of Chemical Technology በኬሚካል ምኅንድስና የPost-Doctoral ፕሮግራም እንዲሁም በUniversity of Maine, USA በ2008 ዓ/ም ክረምት መርሃ ግብር በፐብሊክ ማኔጅመንት የማንዴላ ዋሺንግተን ፌሎውሺፕ ፕሮግራምን ተከታትለዋል፡፡

ዶ/ር አክበር በቻይና ባዮ ጋዝ አሶሴሽን እና በኢንተርናሽናል ባዮ ጋዝ አሶሴሽን በቻይና ቤጂንግ በ2007 እና 2010 ዓ/ም ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ የምርምር ጽሑፋቸውን ያቀረቡ ሲሆን በወላይታ ሶዶ የኒቨርሲቲ ተዘጋጅቶ በነበረው በ2011

ዓ/ም 8ኛውና በ2013 ዓ/ም 9ኛው ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ላይ በመሪ የምርምር ወረቀት አቅራቢነት/Lead Paper Presenter/ ተሳትፈዋል፡፡

ዶ/ር አክበር ከ1998 ዓ/ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተለያዩ የምርምር ሥራዎች እያገለገሉ ሲሆን 47 የምርምር ጽሑፎችን በግልና በቡድን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በአማካሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ዶ/ር አበራ ኡንቻ እና ዶ/ር አክበር ጩፎ በውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ፣ ሳይንቲፊክ ጆርናሎች ላይ በተፈለገው መጠን የምርምር ሥራዎችን በማሳተም፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ጉዳዮች ተሳትፎ እና ሌሎችም በዩኒቨርሲቲው ያከናወኗቸው ተግባራት ተገምግመው አመርቂ ውጤት በማስመዝገባቸው የማዕረግ ዕድገቱን ማግኘት ችለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት