Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በነርሲንግ እና የሕክምና ፕሮግራሞች ላይ ሐምሌ 7/2014 ዓ/ም የፕሮግራም ዕውቅና/Accreditation/ የውጪ ግምገማ አካሂዷል፡፡

የኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በትምህርት ሚኒስቴርና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የፕሮግራም ዕውቅና/Accreditation/ ለማግኘት በተያዘው ዓመታዊ ዕቅድ መሠረት ከዚህ ቀደም በኮሌጁ አምስት ፕሮግራሞች ላይ የውስጥ ግምገማ መደረጉን አስታውሰው ከፕሮግራሞቹ መካከል የነርሲንግ እና የሕክምና ፕሮግራሞች ባመለከቱት መሠረት የውጪ ግምገማ መደረጉን ገልጸዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

እንደ ዶ/ር ታምሩ ግምገማው በተቀመጠለት መለኪያ /Standard/ መሠረት የሚከናወን ሲሆን የውስጥ ግምግማውን ሲያጠናቅቁ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው አካል ደረጃቸውን ያሳውቃል፡፡ በግምገማው የተለዩ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና ደካማ ጎኖችን በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ በተዋረድ እንዲፈቱ ለማስቻል እንዲሁም ተመራጭ ፕሮግራሞችን በማሳደግ ዝግጁ ለመሆን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የውስጥ ግምገማው የትምህርት ፕሮግራሞችን በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር የጎላ ሚና ይጫወታል ያሉት ዶ/ር ታምሩ በመሆኑም ግምገማው ተማሪዎች የሚመረቁበት ፕሮግራም ደረጃውን የጠበቀ የትምህርት ይዘት እንዲኖረው፣ ብቁ ምሩቃንን ለማፍራትና ተፈላጊነታቸውን ለመጨመር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኮሌጁ የነርሲንግ ት/ቤት ዲን ወ/ሮ ሕይወት ታደሰ በበኩላቸው የውስጥ ግምገማው ተጠናቆ ከውጪ በሚያረጋግጡ ቡድኖች በተደረገው ግምገማ ጥሩ ግብረ መልስ /Feedback/ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ በግብረ መልሱ በቀጣይ ማሻሻያና ጠንካራ ሥራ የሚፈልጉ ቦታዎችንም አሳይተውናል ብለዋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የነርሲንግ መምህርና የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር አባል አድማሱ በላይ ግምገማው በነርሲንግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ከመማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት አንጻር ምን እንደሚመስል የዳሰሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢፌዲሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ለውስጥ ግምገማ ያዘጋጀው የመገምገሚያ ቅፅ 9 ንዑሳን ክፍሎችና 190 የደረጃ መለኪያዎች/Standards/ ያሉት መሆኑን ጠቅሰው በኮሌጁ የተከናወነው ግምገማም ይሄን መሠረት አድርጎ ነው ብለዋል፡፡ ከግምገማው በኋላ የነርሲንግ እና የሕክምና ፕሮግራሞች በባለሥልጣን መ/ቤቱ ዕውቅና እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

በኢፌዲሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የዕውቅና አሰጣጥ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታምራት ኃይሌ በበኩላቸው እንደገለጹት የነርሲንግ እና የሕክምና ፕሮግራሞች ዕውቅና እንዲሰጣቸው በፈቃደኝነት ለመገምገም ባመለከቱት መሠረት ያላቸውን ዝግጅት በማየት በተሰጣቸው የማስተካከያ ጊዜ ከኮሚቴዎች ጋር በመሆን በዶክመንትና በተግባር ሥራዎችን አጠናቀው ከባለሥልጣን መ/ቤቱና ከቦርድ ማኅበራት ለተዋቀረው ኮሚቴ ሪፖርት ሲያቀርቡ ዕውቅና ወይም የማሻሻያ ጊዜ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት