Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለውስጥና የውጪ ግንኙነት ባለሙያዎቹ በ‹‹Intercultural Communication›› እና ‹‹Branding›› ዙሪያ ሐምሌ 12/2014 ዓ/ም ሥልጠና አዘጋጅቷል፡፡ ሥልጠናውን በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል መምህርት ኺርጄ ዲንኺማንስ/Geertje Dingemanse/ ሰጥተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ የበይነ-ባህላዊ ተግባቦት/Intercultural Communication/ ክሂሎት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገራት የባህልና አኗኗር ልዩነቶችን ተረድቶ ከሰዎች ጋር በቀላሉ ለመግባባት የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተለያየ ባህል ያላቸውን ሰዎች ያቀፈ እንዲሁም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሠራ እንደመሆኑ ለዕለት ከዕለት ግንኙነትም ሆነ ለተቋማቱ የጋራ ሥራዎች የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎችን የበይነ-ባህላዊ ተግባቦት ክሂሎት ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲውን በተገልጋዮች አእምሮ ሊቀርጽ የሚችል መገለጫ/Brand/ በመፍጠር ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን የመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ማኅበረሰብ ጉድኝት፣ ቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን በሰፊው ለማስተዋወቅ ብሎም ከአጋር ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ጉጉት ለመፍጠር የብራንዲንግ/Branding/ ዕውቀት አስፈላጊ መሆኑን አቶ በድሩ ተናግረዋል፡፡

አሠልጣኝ ኺርጄ ዲንኺማንስ/Geertje Dingemanse/ እንደገለጹት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሠሩበትና ከብዙ የውጪ ሀገራት ተቋማት ጋር ግንኙነቶች ያሉት እንደመሆኑ የተግባቦት አቅሙን አሳድጎ የኢትዮጵያን መልካም እሴቶች በመጠበቅና ከተለያዩ ሀገራት መልካም ልምዶችን በመቅሰም ተወዳዳሪ ለመሆን መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ተቋሙ በውሃ ምኅንድስናና ሌሎችም ዘርፎች የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው ነባር ተቋም በመሆኑ ዝናውን የሚሸከም ተቋማዊ መገለጫ/Brand/ ያስፈልገዋልም ብለዋል፡፡ ለዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች መሰል ሥልጠናዎችን መስጠት ባለሙያዎቹ ያላቸውን የተግባቦት አቅም በማሳደግ ውጤታማ የተግባቦት ሥራ እንዲያከናውኑ ብሎም ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ተቋማት ጋር የጀመራቸውን ግንኙነቶች እንዲያጠናክርና አዳዲስ ግንኙነቶችን እንዲመሠርት እንደሚያግዘው አሠልጣኟ ገልጸዋል፡፡

በሥልጠናው የበይነ-ባህላዊ ተግባቦት ምንነት፣ የተለያዩ ሀገራትን ባህል፣ ልምድና ገጽታ ማወቅ ለበይነ-ባህላዊ ተግባቦት ያለው ፋይዳ፣ የሀገራት መልካም እሴቶች የሚፈጥሩት ቁርኝት፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን የሚገልጹ አሁናዊ ሁኔታዎችና ተቋሙን ለማስተዋወቅ የሚረዱ መንገዶች በሥልጠናው ተዳስሰዋል፡፡ ሥልጠናው የራስ መፈተሻ ጥያቄዎች/Self-Test Questioner/፣ የቡድን ውይይቶች እና አጫጭር የማሳያ ጭውውቶችን ያካተተ ሲሆን በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ለሠልጣኞችና ለአሠልጣኟ የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት