Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ትምህርትና የሥነ-ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት በከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ ግብር ያሠለጠናቸውን 150 ወንድ እና 48 ሴት በድምሩ 198 ሠልጣኝ መምህራን ሐምሌ 16/2014 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በሀገራችን የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከታችኛው ደረጃ ጀምሮ በፍኖተ ካርታ መሠረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው ለትግበራው መሳካትም የመምህራን ሚና ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሥልጠናው መምህራን አመለካከት፣ ዕውቀትና ክሂሎትን አጣምረው እንዲሁም ጥሩ የማስተማሪያ ዘዴን ታጥቀው እንዲሠሩ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ ሠልጣኞችም ሆነ አሠልጣኞች ከማስተማር ሥራ ጎን ለጎን በትዕግስትና በቁርጠኝነት ለማጠናቀቅ በመብቃታቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ለተማሪዎች የሚተላለፈውን መልዕክት በቀላሉ ለማስረጽ ከሙያዊ ችሎታ ባሻገር ብቁ የማስተማር ክሂሎት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው የተሻለ መምህር ለመሆን በሠለጠኑበት ርዕሶች ዙሪያ ተጨማሪ ጽሑፎችን በማንበብ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ ለሠልጣኞች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የከፍተኛ ዲፕሎማ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ የዓለምወርቅ አበራ በሥልጠናው ቆይታ በመማር ማስተማር ክሂሎት ዙሪያ የዕቅድ አዘገጃጀት፣ ተከታታይ ምዘና፣ የመርጃ መሳሪያ አዘገጃጀት፣የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴ፣ በክፍል ውስጥ የተማሪዎች ቁጥጥርና የተለያዩ የተግባር ምርምሮች መሥራት ላይ ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሠለጠኑባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በ1ና 2 ደረጃ ት/ቤቶች ተገኝተው ለተማሪዎች ድጋፍ መስጠታቸውንና ሥራዎቹ ተሰንደው ለዕይታ መቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡

የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከ1999 ዓ/ም ጀምሮ መምህራንን በከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ ግብር እያሠለጠነ ሲሆን እስከ አሁንም ከ1,650 በላይ ሠልጣኞችን ማፍራት ተችሏል፡፡ የከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ ግብር የመምህራንን ዕውቀት፣ ክሂሎት እና አመለካከት በማሳደግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የመማር ማስተማር ሥራ ጥራት እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን አቶ አንለይ ገልጸዋል፡፡

በሂደቱም ለሀገር የሚጠቅም ብቁ፣ አምራች፣ ተወዳዳሪና ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚወጣ ዜጋን ማፍራት ዋነኛ ግቡ ነው ብለዋል፡፡ መምህራኑ በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት፣ ክሂሎትና የአመለካከት ለውጥ ለራሳቸውና ለተማሪዎቻቸው ውጤታማነት እንዲያውሉ በት/ቤቱ ስም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሥልጠናውን ካጠናቀቁ መምህራን መካከል የሳውላ ካምፓስ መምህር የሆኑት አቶ ኢያሱ ማርቆስ የተለያዩ ተማሪዎችን ጠባይ ለይቶ መያዝና ማስተዳደር፣ ከተማሪዎች ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር፣ የማስተማሪያ መርጃ መሳሪያዎችና የምዘና ዘዴዎች አጠቃቀም እንዲሁም ሥነ ምግባርን በማጎልበት በዕውቀትና በአመለካከት ለተማሪዎች መልካም አርአያ መሆንን በተመለከተ ሰፊ ትምህርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ ሠልጣኝ ዶ/ር ኢየሩሳሌም በየነ በሙያና በሥነ ምግባር በቅተን ተማሪዎቻችን ያለባቸውን ክፍተት በመለየት ማስተማር የምንችልባቸውን ዘዴዎች ማየት ችለናል ብለዋል፡፡በመርሃ ግብሩ መጨረሻም ለአሠልጣኞች የምስክር ወረቀትና ለተመራቂ መምህራን የከፍተኛ ዲፕሎማ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት