Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ዶፕላር አልትራሳውንድ ማሽን ለአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሐምሌ 15/2014 ዓ/ም አበርክቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው በዞኑ ከሚገኙ የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር የዕውቀት ሽግግርን ከመፍጠር አኳያ በመደጋገፍ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ከዞኑ ጤና መምሪያ ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር በዞኑ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ሆስፒታሎችን እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሆስፒታሎች አንዱ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ለሆስፒታሉ የተበረከተው ማሽን ለታካሚዎች ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በተለይ በዩኒቨርሲቲው ለሚሠለጥኑ የሕክምና ተማሪዎች በቂ የተግባር ልምምድ አድርገው ክሂሎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለያየ ወቅት በቁሳቁስ ከመደገፉ በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ መምህራን የሆኑ ስፔሻሊስት ሐኪሞች በሆስፒታሉ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያደርግ መሆኑንና የሆስፒታሉን የጤና ባለሙያዎች ዕውቀትና ክሂሎት ለማሳደግ የትምህርት ዕድልና ሥልጠናዎችን እንደሚያመቻች ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ታየ ዩኒቨርሲቲው በዞኑ ለሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት የባለሙያ እገዛና የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያበረከተው ዘመናዊ ዶፕላር አልትራሳውንድ ማሽን የአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋ ማኅበረሰብ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ የሚያወጣውን ተጨማሪ ወጪ ለመቀነስ የጎላ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አንተነህ ካሳዬ እንደገለጹት በሆስፒታሉ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ከዩኒቨርሲቲው በመምጣት ሙያዊ ድጋፍ ማድረጋቸው በሆስፒታሉ በየጊዜው የሚያጋጥመውን የባለሙያ እጥረት በተወሰነ መልኩ እየቀረፈ ይገኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲውም ሆነ የሆስፒታሉ ዓላማ ኅብረተሰቡን ማገልገል በመሆኑ በቀጣይ ሌሎች በሆስፒታሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንደሚሠሩም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በርክክብ መርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው፣ የዞኑ ጤና መምሪያና የሆስፒታሉ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት