Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና በመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ትብብር በግንባታ፣ በምክር አገልግሎት ግዥ፣ በውል አስተዳደርና ንብረት አያያዝ ዙሪያ ከነሐሴ 4-7/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናና የተሞክሮ ልውውጥ መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልደአብ ደምሴ የሥልጠናው ዓላማ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማጋራትና ግንዛቤ በማስጨበጥ የግዥ አሠራሮች እንዲሻሻሉ እንዲሁም ባለሙያዎቹ የአመለካከት ለውጥ አምጥተው የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ እንዲችሉ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የግዥ ሥራ ጊዜ የማይሰጥና ውስብስብ በመሆኑ የሚሻሻሉ አዋጆችና የመመሪያ ለውጦችን በማየት ፈጻሚዎች በመተባበር እና ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎ በመሥራት ኃላፊነታቸውን መወጣትና ራሳቸውን ማሻሻል እንደሚገባቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው መንግሥት በየዓመቱ ለግዥ አገልግሎት በሚመድበው ትልቅ በጀት በመጠንና በጥራት የተፈለገውን ንብረት ወይም አገልግሎት ግዥ በመፈጸምና በአግባቡ በማስተዳደር በተማሪ፣ በተቋምና በሀገር ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመጠበቅ ግዴታ የግዥ አገልግሎትና ንብረት አስተዳደር ዘርፍ መሆኑን በመገንዘብ ባለሥልጣን መ/ቤቱ በየዓመቱ ለዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች፣ ለዘርፉ ሠራተኞችና ለጨረታ አጽዳቂ ኮሚቴዎች የአቅም ማጎልበቻ የተግባር ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮዎቹን በውጤታማነት እንዲወጣ የግዥ ዘርፍ ትልቅ ሚና አለው ያሉት ፕሬዝደንቱ ግዥ በጊዜ ተፈጽሞ አስፈላጊ ግብዓቶች በሚፈለገው ጥራትና መጠን ካልቀረቡ በትምህርትና የምርምር ሥራዎች ውጤታማነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርና በሀገር እድገት ላይም ጉዳት የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ለዩኒቨርሲቲዎች አሠራር መሻሻልና ለትምህርት ሥራ ውጤታማነት በትኩረት እየሠራ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎችም በበኩላቸው ከብክነት የጸዳ ሥራ በጊዜና በመጠን በመፈጸም ለሀገር ልማት መፋጠን በጋራ እንዲሠሩ ፕሬዝደንቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አማካሪ አሠልጣኝ አቶ ነጋሽ ቦንኬ እንደገለጹት በግንባታ ግዥና በምክር አገልግሎት ላይ የዋጋ ማስተካከያ፣ መዘግየት፣ የዲዛይንና ሌሎችም የአሠራርና የአገልግሎት ክፍተት መኖሩን ጥናቶች ያሳዩ ሲሆን ችግሮቹ ተቀርፈው የተሳካ ግዥ እንዲፈጸም ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮዎቻቸውን ማቅረባቸው እርስ በእርስ እንዲማማሩ ያደርጋቸዋል፡፡

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሕግ ባለሙያ ወ/ሮ ስምረት ሙሉጌታ የግዥ ባለሙያዎች ወጥ የሆነ መረዳት እንዲኖራቸው ታስቦ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸው ከሥልጠናው በኋላ ቅሬታዎችና የኦዲት ግኝቶች እንደሚቀንሱና ባለሙያዎችም የዕውቀት ደረጃቸውን ከፍ በማድረግ ጥራት ያለው ግዥ እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የሥልጠናው ተሳታፊ ወ/ሮ መሠረት ተካ ከሕግ ጋር የሚጣረሱ ነገር ግን መሠራት ያለባቸውን አንዳንድ ሥራዎች አዋጅና መመሪያዎችን ተጠቅመን እንዴት መሥራት እንዳለብን ከሥልጠናው ዕውቀት አግኝተናል ብለዋል፡፡ ባገኙት ዕውቀት መሠረት ቀጣይ ሥራዎችን ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ አክለውም የግዥ ሥራዎች ከአመራሮች በሚመጣ ትእዛዝ የሚሠሩ በመሆኑ ሥልጠናው ከባለሙያው ባሻገር ለአመራሮችም ቢሰጥ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሥልጠናው የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የጨረታ አጽዳቂ ኮሚቴዎች፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የግንባታ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት