Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምኅንድስና እና ሒሳብ /Science, Technology, Engineering & Maths – STEM/ ማዕከል ከዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝትና ከተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬቶች እንዲሁም ከ ‹‹STEM Power›› መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ከጋሞ፣ ጎፋና ኮንሶ ዞኖች እና ከደራሼ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ 291 ከ7ኛ- 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ሒሣብ፣ ኤሌክትሮኒክስና ICT ትምህርቶች ከሐምሌ 15 - ነሐሴ 28/2014 ዓ/ም ሲሰጥ የቆየውን የሥልጠና መርሃ ግብር አጠናቋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምኅንድስና እና ሒሳብ ዘርፎች ባገኙት ዘርፈ ብዙ ዕውቀትና የፈጠራ ሥራዎች ልምምድ መነሻ በማድረግ የበለጠ ለመሥራት እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡ በተለይም ሠልጣኞቹ የጊዜ አጠቃቀም ላይ ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን እንደሚሠሩ አልጠራጠርም ብለዋል፡፡

ዶ/ር ዳምጠው ባለፉት ረዘም ያሉ ዓመታት ተማሪዎች መብራት፣ ትራንስፖርት፣ ቤተ ሙከራዎችና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችና ምቹ ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ መማራቸውን ተናግረው በአሁኑ ጊዜ የተሻሉ ምቹ ሁኔታዎች ባሉበት መማራቸው እድለኛ የሚያደርጋቸው በመሆኑ በተመቻቸው እድል ሀገርን የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ ሥራዎችን እንዲሠሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ሥልጠናዎች መካከል በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምኅንድስና እና ሒሳብ ማዕከል በክረምት፣ በሴሚስተር ረፍትና በሳምንት መጨረሻ የሚሰጠው ሥልጠና አንዱ ሲሆን በ2014 ዓ/ም የክረምት መርሃ ግብር 291 ተማሪዎች ሠልጥነዋል፡፡ በሀገራችን የትምህርት እድገት ደረጃ አበረታች ቢሆንም ግድፈቶች ያሉበት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ተማሪዎች በባህርይ፣ በዕውቀትና በክሂሎት እንዲያድጉ በሚያስችል መልኩ መደራጀቱን ማረጋገጥ የዩኒቨርሲቲዎች ድርሻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የማዕከሉ አስተባባሪ ዶ/ር ብንያም ወንዳለ ማዕከሉ የተመረጡ ተማሪዎች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምኅንድስና እና በሒሳብ ትምህርቶች የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ የሚታገዙበትና የሚበረታቱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሀገራት እድገት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምኅንድስና እና ሒሳብ ላይ መሠረት ያደረገ ነው ያሉት አስተባባሪው ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በተለመደው መደበኛ ክፍል የመማር፣ የመመራመር እና ይበልጥ የማወቅ ፍላጎታቸውን ማሟላት ስለማይቻል በነባራዊው ሁኔታ ተውጠው እንዳይቀሩና ተሰጥኦቸውን ለሀገር እድገት እንዲያውሉ ማእከሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎች በየሚማሩባቸው ት/ቤቶች ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት ባይኖርም በዕውቀት፣ በአስተሳሰብና በአመለካከት እንዲያድጉ እንዲሁም በቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ብቁ እንዲሆኑ ሥልጠናው መዘጋጀቱንም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ብንያም ማዕከሉ ‹‹ማንኛውም ልጅ ተመራማሪ ነው›› /Inside Every Child there is a Scientist/ በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2009 ‹‹Foka STEM Center›› በሚል መጠሪያ በቢሾፍቱ ከተማ በትውልድ እስራኤላዊ በዜግነት አሜሪካዊ በሆኑት ማርክ ጌልፋንድ /Mark Gelfand/ ተመሥርቷል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ ሀገር አቀፍ መመሪያ ወጥቶለት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹STEMpower›› በሠራለት የኮምፒውተርና ኤሌክትሮኒክስ ቨርቹዋል ቤተ ሙከራ በ2013 ዓ/ም መጨረሻ ተቋቁሞ ሥራዎችን እየሠራ መቆየቱን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ በማዕከሉ በ2014 በሴሚስተር ዕረፍት ከ7ኛ-8ኛ ክፍል ለሚማሩ 99 ተማሪዎች፣ በሳምንት መጨረሻ ቀናት ከ9ኛ-12ኛ ክፍል ለሚማሩ 54 ተማሪዎችና በክረምት መርሃ ግብር ከ7ኛ-12ኛ ክፍል ለሚማሩ 291 ተማሪዎች ሥልጠና መሰጠቱን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ የመምህራንና የትምህርት አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሻራ ሻታ እንደገለጹት ዓለም ከደረሰችበት እድገት አንጻር ሥልጠናው በተገቢው ጊዜ የተሰጠ ሲሆን ተማሪዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምኅንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶች ዕውቀት እንዲጨብጡ ያስቻለና የዩኒቨርሲቲ ሕይወትን በጥቂቱ እንዲያዩ ያደረገ ነው፡፡ ሥልጠናው ተማሪዎች የራሳቸውን የፈጠራ ሥራ እንዲሠሩና እርስ በእርስ እንዲማማሩ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቡርጂ ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ቦዳ በበኩላቸው ከ7ኛ-12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የፈጠራ ሥራቸው የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ዕውቀትና ችሎታቸው በቴክኖሎጂ ቢደገፍ የተሻለ ሥራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በሁሉም ት/ቤቶች ቤተ ሙከራዎችን በተሻለ ሁኔታ በማደራጀት የፈጠራ ክሂሎታቸውን እንዲያሳድጉና ለራሳቸውም ለሀገርም የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለብን ብለዋል፡፡

የገረሴ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪና የፈጠራ ባለሙያ የሆነው ተማሪ ቴዎድሮስ ማቲዮስ መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በማይደርስባቸው አካባቢዎች በትምህርት ቤቶችና በጤና ጣቢያዎች በአካባቢው በሚገኝ ውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል የፈጠራ ሥራ ሠርቷል፡፡ የፈጠራ ሥራው ለመብራት አገልግሎትና ለምግብ ማብሰያነት በመዋል የማገዶ ወጪ የሚቀንስና በጭስ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን የሚያስወግድ እና ሌሎችም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታዎችን በመስጠት የኅብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል የሚያደርግ መሆኑን ተማሪ ቴዎድሮስ ተናግሯል፡፡ ተማሪ ቴዎድሮስ በተለያዩ ጊዜያት ድንቅ ፈጠራዎች የሚሠሩ ቢሆንም አቅም ያላቸውና ዕድሉን ያላገኙ ተማሪዎች ሥራቸው መሬት ሳይወርድ እንዳይቀር ፈጠራቸው ተግባራዊ ሆኖ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታበት መንገድ ቢመቻች መልካም ነው ብሏል፡፡

በሥልጠናው መዝጊያ መርሃ ግብር በተማሪዎች የተሠሩ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች የተጎበኙ ሲሆን ሥልጠናውን ተጠቅመው የላቀ ፈጠራ ለሠሩ ተማሪዎች ልዩ ሽልማት እንዲሁም ለሁሉም ሠልጣኝ ተማሪዎች የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

 የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት