Print

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስ/ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ከሆስፒታሉ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች በወባ በሽታ ምርመራና ሕክምና አሰጣጥ አዳዲስ አሠራሮች ዙሪያ ከጥቅምት 18-19/2015 ዓ/ም የሁለት ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ኮሌጁ በተለያዩ ጤና ተቋማት ለሚያገለግሉ ለሕክምናና ጤና  ባለሙያዎች የረጅምና የአጭር ጊዜ የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን በመስጠት አቅማቸውን ማጎልበትና ከአዳዲስ የዘርፉ አሠራሮችና ግኝቶች ጋር የማስተዋወቅ ሥራን  በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም አንፃር በኮሌጁ የሚገኘው የሙያ ማሻሻያ ማዕከል በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ከደቡብ፣ ከሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተወጣጡ የመስኩ ባለሙያዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠናዎች ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ማዕከሉ ሥልጠና ከማዘጋጀትና ከመስጠት ባሻገር ለጤና ባለሙያዎች ለሙያ ዕድሳት ማገልገል የሚችል የምስክር ወረቀት የመስጠት እንዲሁም ሌሎች መሰል ተቋማትን የመገምገምና ዕውቅናና ዕድሳት የመስጠት ኃላፊነት በጤና ሚኒስቴር የተሰጠው መሆኑንም ዶ/ር ታምሩ ጠቅሰዋል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት ማዕከሉ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጠና መስጠቱን የገለጹት ዶ/ር ታምሩ ማዕከሉ እንደ ሀገር በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በቀጣይ የሕክምናውን ሴክተር የሚያሻሽሉ የተለያዩ መሰል ሥልጠናዎችን መስጠቱንና ሌሎች ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ ተ/ፕ ፈለቀ ገ/መስቀል በበኩላቸው ሥልጠናው በዋናነት በወባ በሽታ ምርመራና ሕክምና አሰጣጥ አዳዲስ አሠራሮች ዙሪያ በማተኮር ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ከሕፃናት፣ ከላቦራቶሪ፣ ከእናቶች፣ ከውስጥ ደዌ፣ ከድንገተኛ፣ ከተመላላሽ ሕክምናና ሌሎች የሥራ ክፍሎች ለተወጣጡ 25 የጤና ባለሙያዎች የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡   ሥልጠናው በዋናነት በሆስፒታሉ በወባ በሽታ ሕክምና አሰጣጥና አስተዳደር ዙሪያ የተደረገን ዳሰሳ ጥናትን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ያወሱት ኃላፊው በዳሰሳ ጥናቱ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማሟላት የሚያስችል ግንዛቤ ለጤና ባለሙያዎቹ በመፍጠር የበሽታውን ሕክምና አሰጣጥ፣ ምርመራና የመከላከል ሥራን ማሻሻል የሥልጠናው ዋነኛ ግብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወባ በሽታ ሕክምና አሰጣጥ አዲስ ፕሮቶክልን ለባለሙያዎቹ ማስገንዘብ ሌላኘው የሥልጠናው ትኩረት ሲሆን በቀጣይ በሥልጠናው የተነሱ አዳዲስ አሠራሮች ተግባር ላይ መዋላቸውን ማዕከሉ ክትትል እንደሚያደርግም ተ/ፐሮፌሰሩ ጠቁመዋል፡፡

ከአሠልጣኞች መካከል የሕፃናት ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪምና የኮሌጁ መ/ር ዶ/ር ሙሉቀን አህመድ የወባ በሽታ ፕላስሞዲየም በተሰኘ ፓራሳይት አማካኝነት የሚከሰትና በወባ ትንኝ ንክሻ ምክንያት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና በዓለማችን ከ5 ዋነኛ ገዳይ በሽታዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 5 የወባ በሽታ ዓይነቶች የሚገኙ መሆኑን የገለጹት አሠልጣኙ ፋልስፋረምና ቫይቫክስ የተሰኙት የወባ በሽታ ዓይነቶች ብቻ በኢትዮጵያ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የወባ በሽታ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመቀነስ ይልቅ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ሙሉቀን ለዚህም በሕክምና ሥራው ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበትና ከአዳዲስ አሠራሮችና ግኝቶች ጋር ማስተዋወቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ከወባ በሽታ ምርመራ፣ መድኃኒት አሰጣጥና አወሳሰድ ዙሪያ የተለያዩ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ የተናገሩት ዶ/ር ሙሉቀን መሰል ሥልጠናዎች ክፍተቶቹ እንዲሟሉና የሕክምና አሰጣጡን በማሻሻል በሽታው የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች ከመቀነስ አንፃር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በውስጥ ደዌ ሕክምና ክፍልና በታካሚዎች ቅበለና ስንብት ክፍል የሚሠሩት ሲ/ር ትንሣኤ ይፍሩ እና አቶ መንግሥቱ ኪፎ በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው ከወባ በሽታ ሕክምና አሰጣጥ አዳዲስና የተከለሱ አሠራሮች ጋር የተዋወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሳይንስ ተለዋዋጭ መሆኑን ያወሱት ሠልጣኞቹ መሰል ሥልጠናዎች ከአዳዲስ የሳይንስ ግኝቶች ጋር ባለሙያው እንዲተዋወቅ ከማድረግ አንፃር የጎላ ሚና ይጫወታሉም ብለዋል፡፡ በሥልጠናው የተገኙት አዳዲስ ዕውቀቶች በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የወባ በሽታ ሕክምና አሰጣጥና አስተዳደር የሚያሻሽሉ መሆኑንና ይህንንም ተግባራዊ ሠልጣኞቹ ለማድረግ እንደተዘጋጁም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

እንደ አወሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2020 ብቻ በዓለማችን 241 ሚሊየን ሰዎች በወባ በሽታ የተያዙ ሲሆን ከነዚህም መካከል 627 ሺ ያህሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች መካከል 95 ከመቶው እንዲሁም ከሟቾች መካከል 96 ከመቶው አፍሪካውያን መሆናቸውን መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ከሟቾች መካከል 80 ከመቶው ደግሞ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት