Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ከዩኒቨርሲቲው ለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር  ለዩኒቨርሲቲው  ካውንስል አባላት ግምገማዊ የሥልጠና መድረክ ጥቅምት 22/2015 ዓ/ም አዘጋጅቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ከ2014 ዓ/ም ዕቅድ አፈጻጸምና ከ10 ዓመቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መነሻነት የ2015 ዓ/ም ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ የግምገማዊ ሥልጠና መድረኩ ዕቅዱንም በስኬት ለመተግበር ያግዝ ዘንድ በአመራርና አስተዳደር፣ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች በለውጥ ተግባራት ማሻሻያ ሥራዎችና  ሌሎች የትኩረት ጉዳዮች ዙሪያ የካውንስል አባላት ወጥ የሆነ አቅጣጫ እንዲይዙና ለ2015 ዓ/ም ዕቅድ አፈጻጻምም ማነቃቂያ እንዲሆን ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ከመድረኩ የሚገኘውን ግብዓት በመጠቀም ወደ ተግባር ለመቀየር የካውንስል አባላት እንዲዘጋጁ አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቃልቦ ባቀረቡት ገለጻ በአመራርና አስተዳደር ዘርፍ በ2015 ዓ.ም ሊከናወኑ ከታቀዱ ተግባራት መካከል በዩኒቨርሲቲው ሠላማዊ መማር ማስተማርን ከማስቀጠል፣ የዩኒቨርሲቲውን መልካም ገጽታ ከመገንባት፣ የዩኒቨርሲቲውን ሀብት ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ከመጠቀምና ተደጋጋሚ ግዥዎችን ከማስቀረት፣ ሴቶችን ከማበረታታትና ወደ መሪነት ከማምጣት አኳያ ያሉ የዕቅድ ተግባራትና ሌሎች ጉዳዮች ተካተው  ውይይት ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የለውጥና መልካም አስተዳዳር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ በፈቃዱ  ባቀረቡት ገለጻ ‹‹የሠራተኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና አሠራርና ውጤት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መለየት›› በሚል ርዕስ በባለሙያዎች ጥናትና ምርምር ተካሂዶ  የተለያዩ ችግሮች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ በኃይሉ ከችግሮቹም መካከል የሠራተኛው የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤት ሥራን መሠረት ያደረገ ያለመሆን፣ የሥራ አፈጻጸም ውጤት ወቅቱን ጠብቆ ያለመሞላቱና ባለሙያዎች ጥንካሬና ድክመታቸውን ለይተው ራሳቸውን እንዲያሻሽሉና ለተሻለ ውጤት እንዲተጉ የሚያስችል ያለመሆኑ እንዲሁም ኃላፊዎች ዕቅዶችን ከባለሙያዎች ጋር ተፈራርመው ያለመሥራት እና አፈጻጸሙን ያለመከታተል እና መሰል ችግሮች በጥናትና ምርምሩ ግኝት ተረጋግጠዋል፡፡ በቀጣይም  የሥራ አፈጻጸም ውጤት የሲቪል ሰርቪስ የሠራተኛ የሥራ መመዘኛ ውጤት ፎርምን መሠረት አድርጎ እንድሞላ ማድረግ፣ ሠራተኛው ዕቅዶችን በወርና በሳምንታት ከፋፍሎ እንዲሠራ ማድረግ፣ የሠራተኛው የሥራ መመዘኛ /ውጤት ተኮር/ ወቅቱን ጠብቆ እንድሞላ ማደረግ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራሞች፣ ክትትልና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ከተቀመጠው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ መነሻነት በአካዳሚክ ዘርፍ በ2014 ዓ/ም ከነበረው በተሻለ ሁኔታ በ2015 ዓ/ም ለማከናወን ከታቀዱ መካከል የትምህርት ጥራት አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ የተቀመጡ ዕቅዶችንና አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችን ለመክፈት የውጭ ግምገማ ለማካሄድ ለመጀመሪያ ዲግሪ 2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ያላቸው፣ ለ2ኛ ዲግሪ 3ኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለ3ኛ ዲግሪ ደግሞ ሙሉ የፕሮፌሰርነትና ከዚያ በላይ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ምሁራን የሚፈለጉ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡  

የዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕ/ጽ/ቤት ልዩ አማካሪ ዶ/ር ነጅብ መሐመድ በመማር ማስተማር ዘርፍ  በ2015 ዓ.ም በትኩረት ለመሥራት ከታቀዱ መካከል የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና አንዱ ሲሆን የትምህርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የቅድመ-ምረቃ ትምህርት መስኮች የመውጫ ፈተና ለማስጀመር ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ሁሉም የተቋማችን ኢንስቲትዩቶች፣ ኮሌጆችና ት/ክፍሎች ወደ ሥራ እንዲሠማሩ፣ የዩኒቨርሲቲው ተፈታኞች፣ መ/ራንና በየደረጃው ያሉ ከፍተኛ አመራር አካላት ሚናቸውን በመለየት ወደ ተግባር እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡ 

በ2015 ዓ/ም ለመሥራት ካቀዷቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የምርምር ፕሮጀክቶች በተገቢው ሁኔታ ተሠርተው መጠናቀቃቸውን መከታተልና ማስፈጸም ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም 650 በሂደት ላይ ያሉ የምርምር ፕሮጀክቶች እንዳሉና በበጀት ዓመቱም አዲስ 200 የምርምር ፕሮጀክቶችን ለመሥራት አቅደው እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም ከሀገር ውስጥና ውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር የሚሠሯቸው የምርምር ፕሮጀክቶችን ቁጥር ቀድሞ ከነበረው ጨምሮ ለመሥራት  ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተስፋዬ ገለጻ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ  በ3ኛ እና 2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የሚሠሩ የምርምር ፕሮጀክቶችን ከመ/ራንና ተመራማሪዎች ጋር በማቀናጀት እያማከሩና እየተመራመሩ ማስተማርና እየተማሩ መመራመር እንዲሁም በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለተማሪዎች መስጠት እንዲቻል ብሎም የምርምር ወጪን በመቀነስ የምርምር ጽሑፎችን በተለያዩ ጆርናሎች ላይ ለማሳተምም አስቻይ ሁኔታዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የ2015 ዓ/ም የማኅብሰብ ጉድኝት፣ የኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር የትኩረት ተግባራትን ዝርዝር ሲያስተዋውቁ መካከል በጨንቻ የሻማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ በከምባ የዲንጋሞ አነስተኛ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ የጋጮ ባባ ወንዝ ድልድይ ሥራ፣ የዶርዜ የጠዬ ወንዝ ድልድይ ሥራ፣ የሻራ የመጠጥ ውሃ እና የሀመሳ መስኖ  ፕሮጀክት፣ የጫኖ የሀሬ ወንዝ መስኖ ቦይ ጥገና እና በአርባ ምንጭ ከተማ በተለምዶው ሳልባጅ ተራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ አደበባይ ማልማት የሚሉት ከዋና ዋናዎቹ  መካከል ይገኙበታል፡፡

በሥልጠናውም  የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት