Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት አማካኝነት በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገው የተዘጋጁ 35 ንድፈ-ሃሳቦች ቀርበው ከጥቅምት 24-25/2015 ዓ/ም ግምገማ ተካሂዶባቸዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለጹት እንደ ዩኒቨርሲቲ  የማኅበረስብ ጉድኝት ሥራዎች ምርምርን መነሻ ማድረግና ውጤታማ የሆኑ ሥራዎች ለኅትመት መብቃት እንዲሁም ወደ ማኅበረሰቡ ወርደው ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አንጻር የኅብረተሰቡን ችግር መፍታትና ኅብረተሰቡ እንዲረካ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነህ አክለውም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን የቀረቡት የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ንድፈ-ሃሳቦች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ሁሉም የኢንስቲትዩቱ መምህራንና ተመራማሪዎች በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራ መሳተፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረ/ፕ አዲሱ ሙሉጌታ በዚህ ዓመት በምርምር እና በማኅበረስብ ጉድኝት ዘርፍ ሊሠራባቸው በሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ንድፈ-ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ በተደረገው ጥሪ መሠረት ከኮምፒውቲንግ፣ ሜካኒካል፣ ሲቪል እና ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ፋከልቲዎች እንዲሁም ከታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል 24 ንድፈ-ሃሳቦች እንዲሁም በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍም 18 ንድፈ-ሃሳቦች ቀርበው 11ንዱ ለግምገማ መቅረባቸውን የጠቆሙት ረ/ፕ አዲሱ ይዘቶቹም በታዳሽ ኃይል፣ ኢነርጂና ግብርናን በማዘመን የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ የሚረዱ ናቸው ብለዋል፡፡

በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ‹‹Application of Solar Box Cooker for Community›› በሚል ርዕስ ንድፈ-ሃሳብ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ፋከልቲ የተርሚናል ኢነርጂ መ/ር ሀብተወልድ አባቡ ከፀሐይ ብርሃን የሚገኘውን ኃይል በመጠቀምና ወደ ኢነርጂ በመቀየር በቀላሉ ምግብን ማብሰልና ሌሎች ሥራዎችን መሥራት ያስችላል ብለዋል፡፡

አክለውም የአካባቢ መራቆትን፣ የደን መመናመንንና የሙቀት መጠንን በመቀነስ የመኖሪያ አካበቢያችን ምቹ እንዲሆን የሚረዳ ሲሆን በዚህ ዓመት ወደ ተግባር በመግባት 30 አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የኮምፒውቲንግና ሶፍትዌር አንጂነሪንግ ፋከልቲ መ/ር ክብረዓብ አዳነ በበኩሉ ‹‹Machine Learning and Deep Learning Based Phishing Websites Detection as Cyber Security Defense Strategy for Ethiopian Institutions›› በሚል ርዕስ ንድፈ-ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን  ጠቀሜታውም  በአሁኑ ጊዜ ኢትያጵያ ውስጥ በመንግሥትና በግል ተቋማት ላይ የሚፈጸመውን ‹‹Phishing›› የሚባለውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚጠቅም ነው ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ   የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፈክ ዳይሬክተርን ጨምሮ የኢንስቲትዩቱ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ ዳይሬክተሮች፣  የፋከልቲ ዲኖችና መ/ራን ተሳትፈዋል፡፡

                                                                                                                                                                                   የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት