Print

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር 16ውን የአፍሪካ ወጣቶች ወርን ‹‹ትምህርትና የወጣቶች ስብዕና ግንባታ›› በሚል ርዕስ ኅዳር 1/2015 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው አክብረዋል፡፡ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዓሉ በአፍሪካ ደረጃ “Breaking the Barriers to Meaningful Youth Participation and Inclusion in Advocacy” በሚል መሪ ቃል እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ‹‹የወጣቶች ንቁ ተሳትፎና ተካታችነት ለስብዕና ልማት›› በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መረሃ-ግብሮች እየተከበር ይገኛል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የአፍሪካ ወጣቶች ወር ወጣቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ውስጥ ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለመዘከር እንዲሁም በቀጣይ የአህጉራችንን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ውስጥ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል በየዓመቱ በተለያዩ የግንዛቤና የንቅናቄ መርሃ-ግብሮች እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች ወር የአፍሪካ ወጣቶች ጉዳዮችን በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በማቅረብ በአንድነት የሚከበርበት፣ የአህጉሩ ወጣቶች እርስ በእርስ ተቀራርበው በራሳቸው፣ በሀገራቸው ብሎም በአህጉራቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የልማትና የሠላም ጉዳዮች ዙሪያ በባለቤትነትና የሚወያዩበትና   ሀገራቸውንና አህጉራቸውን የተሻለ ለማድረግ ቃል ኪዳናቸውን የሚያዱስበት ነውም ብለዋል፡፡

በሀገራችን በዓሉ ከጥቅምት 22/2015 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከበረ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ ትምህርትና የወጣቶች ስብዕና ግንባታ በሚል ርዕስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የግንዛቤና የንቅናቄ መድረክ የዚሁ ሀገራዊ መርሃ -ግብር አካል ነው ብለዋል፡፡ ወጣትነት በርካታ አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ስሜታዊ፣ አዕምሮዊ ለውጦች የሚስተዋሉበትና ለቀጣይ ሕይወት መሠረት የሚጣልበት ዕድሜ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ኤርጎጌ በየደረጃው ያሉ የትምህርት ተቋማት ወጣቶች በዕውቀትና በሥነ-ምግባር የታነጹ፣ ስብእናቸው የተስተካከለ፣ ከአጋጉል ልማዶችና ሱሶች የራቁ እንዲሆኑ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የትምህርቱ ሴክተር አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንና ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ መፃኢ ዕድሏን መወሰን ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወት የሚችሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕድገትና ብልጽግናዋን ማረጋገጥ የሚያስችል እምቅ አቅም ያላቸው የበርካታ ሚሊየን ወጣቶች ምድር ነች ብለዋል፡፡ ይህን ግዙፍ የማኅበረሰብ ክፍል በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የሀገራችንን ቀጣይነት ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተብትቦ ከያዛት የድህነት ማቅ ማላቀቅ እንደሚቻልም ፕ/ር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ በሀገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተሠሩ ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴርም ሀገር ተረካቢ ለሆነው ወጣት ትኩረት በመስጠት በአግባቡ የሠለጠነ፣ ከዘመኑ የዓለም ወጣቶች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርግ ዕውቀት ያለው፣ በሥነ-ምግባሩ የተመሰገነ፣ ምክንያታዊ ስብዕና ያለው ወጣት ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ሚኒስትሩ አውስተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ‹‹ ወጣቶች፣ የወደ ፊት ስኬታችሁ የሚወሰነው በዛሬ ጥረታችሁ በመሆኑ የዛሬ አፍላ ዕድሜያችሁን ከፍ በሚያደርግ ተግባር፣ ዕውቀት፣ ክሂሎት በመቅሰም ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል›› ሲሉም መልዕካታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብትና ለኑሮ ተስማሚ በሆነ የአየር ንብረት የታደለች ሀገር ብቻ ሳትሆን በሚሊየን የሚቆጠሩ በርካታ በአምራች ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ያሏት ሀገር መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡ በሰው ልጆች ዕድገት ሂደት ውስጥ የወጣትነት ዕድሜ ዘመን አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠርና ትላልቅ ነገሮችን ለመሥራት የሚያስችል ጠንካራ የሆነ አካላዊና አዕምሮአዊ አቅም ያለበት ዕድሜ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዳምጠው ይህንን የወጣትነት አቅም በአግባቡ መጠቀም ከታቻለ ከግለሰብ ባሻገር ለማኅበረሰብ ለወጥና ብልጽግና የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ወጣቶች ወይም ተማሪዎች የዓላማ መሪነት፣ የአዎንታዊነት፣ የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመተባበር፣ የበጎነት፣ የምክንያታዊነት፣ የባለቤትነት፣ የአሳታፊነት፣ የብዝኃነት፣ ቁርጠኝነትና መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ የመወሰን  ዕሴቶችን መታጠቅ ይገባቸዋል ያሉት ፕሬዝደንቱ ወጣቶች ያላቸውን ችሎታ በማጎልበትና  ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለሀገራቸው ሁለተናዊ ለውጥና ብልጽግና ሊተጉ ይገባልም ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት “Population Fund Agency” በመወከል መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ሚስ ሱዛን ማንዶንግ/Ms Suzanne Mandong/ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ወጣቶች አብዛኛውን የሕዝብ ቁጥር የሚይዙ መሆኑን ገልፀው ወጣቶች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንትንና ውሳኔ ሰጪነትን ማጎልበት እንዲሁም ተሳትፎን ማሳደግ  ይገባል ብለዋል፡፡ ወጣቶች የዛሬም የነገም መሪዎችና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ሃሳቦች ፈጣሪዎች ናቸው ያሉት ሚስ ሱዛን ወጣቶች እንደ አፍሪካ ባሉ አህጉሮች ድኅነትን ለመቀነስና የሕዘባቸውን ኑሮ ከማሻሻል አንፃር እንዲሁም የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ለማሳካት ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል፡፡ ተቋማቸው በወጣቶች አቅም ግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በሀገሪቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ ሲሆን በቀጣይም ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደሚሠራም አውስተዋል፡፡

በዕለቱ መርሃ-ግብር ላይ ወጣት ሥነወርቅ ታዬና ወጣት ሃና ኃይሉ በትምህርትና ስብእና ግንባታ እንዲሁም በጊዜ አጠቃቀም ዙሪያ አነቃቂ ንግግር ያቀረቡ ሲሆን የኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤናና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞና አባላት፣ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ደኤታዎች፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴና የዞኑ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንዲሁም  ከአካባቢውና ከሌሎች የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተጋበዙ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት