Print

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሙያ ማበልፀጊያ ማዕከል ከጋሞ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ጋርና ከደረጃ ዶት ኮም/Dereja.Com Academy/  ከተባለ የግል ድርጅት ጋር በመተባባር ለአርባ ምንጭ ከተማ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ስለደረጃ ዶት ኮም አካዳሚ አክስለሬተር ፕሮግራም/Dereja.Com Academy Accelerator Program/ ሥልጠና ከኅዳር 3/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ወራት  እየሰጠ ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሙያ ማበልፀጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ  ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮዎች መካከል አንዱ የማኅበረሰብ ጉድኝት በመሆኑ ይህንን ለማሳካት ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲዎች ለአዲስ ተማራቂ ተማሪዎች ከሚሰጠው ሥልጠና በተጨማሪ ከጋሞ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ጋር በመተባባር ለመጀመሪያ ጊዜ በአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ለሆኑና በ2014 ዓ.ም በተለያዩ የሙያ መስኮች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ሥራ ፍለጋ ላይ ላሉ ወጣቶች ስለደረጃ ዶት ኮም አካዳሚ አክስለሬተር ፕሮግራም የ3 ወር ሥልጠና ለመስጠት በታቀደው መሠረት ሥልጠናው ገቢራዊ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡ ሠልጣኞች የራሳቸውን የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉና ተቀጣሪ ሆነው መሥራት የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ዕውቀት በማስጨበጥ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸውና የ3 ወሩን ፕሮግራም በትክክል ተከታትለው ላጠናቀቁ ሠልጣኖች ድርጅቱ  የሥራ ዕድል እንደሚያመቻች አስተባባሪዋ ጠቁመዋል፡፡

የደረጃ ዶት ኮም ሥልጠና አስተባባሪና አሠልጣኝ አቶ መኮንን መንገሻ  እንደተናገሩት ሥልጠናው የደረጃ ዶት ኮም  አካዳሚ አክስለሬተር ፕሮግራም በሚል ይዘት ለ3 ወራት በበይነ-መረብ/Online/ የሚሰጥ ሲሆን በዋናነት 3 ፕሮግራሞች ሰዋዊ ክሂሎት/Soft Skill/፣ ሙያዊ ክሂሎት /Professional Skill/ እና የሙያ ምክክር /Career Guidance/ ያካተተ ነው፡፡ ሠልጣኞች በአጠቃላይ 8 ሞጁሎችን ማጠናቀቅና ከታዋቂ የሙያ አማካሪዎች ጋር በመካከር ልምድ እንዲወስዱ እንደሚደረግ አቶ መኮንን ጠቁመዋል፡፡  ሥልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው ለሚያጠናቅቁ ሠራተኞች በደረጃ ዶት ኮምና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ያንግ አፍሪካን ዎርክስ ፕሮግራም የደረጃ ዶት ኮም አካዳሚ አክስለሬተር ፕሮግረም አጠናቀዋል የሚል ምስክር ወረቀት እንደሚሰጥና ከድርጅቱ ጋር በትብብር ከሚሠሩ ካምፓኒዋች ጋር በማገናኘት የሥራ ዕድል እንዲያገኙና የግላቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ እንደሚያመቻች እንዲሁም ለውድድር ክፍት በተደረጉ የሥራ ማስታወቂያዎችም ሲወዳደሩ ሥልጠናውን ካልወስዱ ተወዳዳሪዎች የተሻለ የመቀጠር ዕድል እንደሚኖራቸው አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡

ወጣት ዝናቡ ቦቆሻ የአርባ ምንጭ ከተማ ሥራ ፈላጊ ወጣት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በባዮሎጂ ትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ ሲሆን ሥልጠናውን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት በተለይ በሰዋዊ ክሂሎት ላይ የተሰጠው ትምህርት ራሱን እንዲያይ፣ ሃሳቡን መግለጽ እንዲችል፣ የሰውን ሃሳብ እንዲረዳና የአስተሳሳብ ደረጃውንም እንዲያሻሽል ረድቶኛል ብሏል፡፡

ሥልጠናው በበይነ-መረብ የሚሰጥ ሲሆን ለ120 የአርባ ምንጭ ከተማ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ከኅዳር 3/2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት