Print

በድጋሚ የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዝደንት ሆነው ስለተመረጡ እንኳን ደስ አልዎት!!

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቀዳሚ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ዋናኛውና ከተወዳዳሪዎች መኃል እንደሚገኝም ገሀድ ነው። ይህ ታላቅ ተቋም፣ የገዘፈ ስሙ እንዲቀጥል፣ ከታሪኩ የተቆራኘው የናኘ ዝናው አብሮት እንዲከርም፣ ዩኒቨርሲቲውን የሚመራው አካል ሚና ወሳኝነት አለው። በተለይም ደግሞ በትምህርት ዘርፉ የሚደረገውን ሪፎርም ከፍፃሜ ለማድረስ፣ ሪፎርሙንም የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት መሪው የአውራ ድርሻ ይኖረዋል።

ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የዩኒቨርሲቲውን ትልቅ ኃላፊነት በመሸከም ላለፉት ዓመታት ያለመታከት፣ ተቋሙን በስሙ ልክ ለማስኬድ ጥረትዎ ቀላል እንዳልነበረ እንገነዘባለን። የዚሁ ትጋትዎ ውጤት የሆነው አዲሱ ሹመትዎም፣ ከቀደመው የላቀ ብርቱ ኃላፊነት ከትከሻዎ ላይ እንዳረፈ ከእርሶ እኩል የምንጋራው ስሜት ነው።

በተለይም እንደተማሪዎች ኅብረት አደረጃጀት በሥራችን መኃል ለሚፈጠሩ አንዳንድ ሳንካዎች እና እንቅፋቶች፣ ለፈጣን ምላሽ የችግራችን አድማጭ እንደሆኑ በዚሁ አጋጣሚ ልንሰጥ የምንፈልገው ምስክርነት ነው።  ኅብረቱ ሊሠራ ያሰበውን ውጥን ከግብ ለማድረስ፣ በእርሶ ዳግም መመረጥ ታላቅ ደስታ እንደተሰማን ስንገልፅልዎ በታላቅ ኩራት ነው።  በድጋሚ እንኳን ደስ አልዎት ማለት እንወዳለን!!

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው፣ በዩኒቨርሲቲው የመሪነት ስፍራ ዳግም መሰየምዎ ለግዙፍ ኃላፊነት እንደታጩ መረዳት እንችላለን። የተማሪዎች ኅብረትም፣ በየትኛውም ዘርፍ የእኛ ድጋፍ ባሻዎ ጊዜ ለመደገፍ ትከሻችንን አስፍተን እንደተሰናዳን መግለጽ እንወዳለን።

በሚቀጥለው ሂደት ላይ ፈጣሪ ከጎንዎ ይሆን ዘንድ እየተመኘን፣ ለሥራዎ ስኬት ዘወትር ከአጠገብዎ እንዳለን አስምረን ማለፍ እንሻለን።

መልካም የሥራ ዘመን ይሁንልዎ፤ ይሁንልን!

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት

ተማሪ ደሳለው ቆለጭ