Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኦቾሎ ቀበሌ በቁንጭር (ቦልቦ)በሽታ ላይ ያከናወነው ታላቅ የምርምር ፕሮጀክት ውጤት  ለማኀበረሰቡ አጋር ተቋማት የማስተዋወቂያ ወርክሾፕ ጥር 26/2015 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የደቡብ ክልል በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበቻ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማሌ ማቴ እንደገለፁት ትኩረት የሚሹ የሀሩራማ አካባቢ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ብዙ ለውጦች የመጡ ሲሆን በትብብር ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች በቀጣይነት ሊካሄዱ ይገባል፡፡ ቁንጭር በሽታን ለማጥፋት ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትብብር መሥራትና የበሽታው ምልክት በሚታይበት ጊዜ ለሚመለከታቸው አካላት የማሳወቅ፣ ሕመምተኞች ሕክምና እንዲያገኙ የማድረግና ስለበሽታው ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ከዩኒቨርሲቲው ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሁለት የ2 ዲግሪ ተማሪዎችና ቤልጂየም ሀገር የሚገኝ “Institute of Tropical Medicine” የተሰኘ ተቋም የተሳተፉበት በቁንጭር (ቦልቦ)በሽታ ላይ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኦቾሎ ቀበሌ ላይ የተከናወነ ታላቅ የምርምር ፕሮጀክት ውጤትን ለማኀበረሰቡ አጋር ተቋማት ለማስተዋወቅ ወርክሾፑ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ ቁንጭር (ቦልቦ)በሽታ በዓለም ጤና ድርጅት ከተለዩ 17 የተዘነጉ የሀሩራማ አከባቢ በሽታዎች አንዱ ሲሆን ከ1962 ዓ/ም ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት ትኩረት ያልተሰጠውና ምንም ዓይነት መፍትሄ ያልተገኘለት በሽታ መሆኑን ተ/ፕ በኃይሉ ጠቅሰዋል፡፡ ቁንጭር በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የስነልቦና ጫና ያስከተለ በሽታ መሆኑንና ምርምሩም በዘርፉ  እንደሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ኤክስኪዩቲቨ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም እንደዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ታላቅ የምርምር ፕሮጀክቶች “Grand Research Projects” ድጋፍ እየተደረገላቸው እየተሠሩ ያሉ ሲሆን በኦቾሎ ቀበሌ ላይ በቁንጭር በሽታ ላይ የተካሄደው የምርምር ፕሮጀክት ሥራም አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ ዩኒቨርሲቲው በተመሳሳይ በማኅበረሰቡ የተለያዩ ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግና አስፈላጊውን በጀት መድቦ በማስጠናት የተገኘውን ውጤት ለማኅበረሰቡ ይፋ እያደረገ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገና በትኩረት እየሠራ ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ተክሉ በኦቾሎ ቀበሌ  በቁንጭር /ቦልቦ/ በሽታ ላይ በተካሄደው ምርምር የተገኘውን ውጤት መነሻ በማድረግ በሽታውን ከአካባቢው ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመረባረብ ሊሠሩ ይገባል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሜዲካል ላቦራቶሪ ትምህርት ክፍል ሜድካል ማይክሮ ባዮሎጂስት አቶ ዳግማዊ ታደሰ በበኩላቸው እንደተናገሩት ምርምሩ የተሠራው ዩኒቨርሲቲው በመደበው 999 ሺህ 650.00 ብር ድጋፍ ሲሆን ጥናቱ የማኅበረሰቡን ዘርፈ ብዙ ችግር የሚፈታ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮና የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የኦቾሎና ጤጌቻ ቀበሌ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣  የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት፣ የምርምር ኤክስኪዩቲቨ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ባለሙያዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት