Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ውኃ አዘል መሬቶችና የተፈጥሮ ምንጮች ላይ ከሚሠራው ‹‹Ethio-Wetlands and Natural Resources›› ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የዓለም ውኃ አዘል መሬቶች (World Wetlands Day) ቀንን አስመልክቶ ጥር 25/2015 ዓ/ም የጋራ ውይይት አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዕለቱ ‹‹Introductory Presentation on Wetland Management Efforts, Sediment Dynamics at lake Abaya››፣ ‹‹Unsustainable Agriculture and its Impact on Lakes and Wetland landslides›› እና ‹‹The Role of Enset for Ensuring Ecosystem Services›› የሚሉ ጥናታዊ ጽሑፎች እና በኢትዮጵያ ውኃ አዘል መሬቶችና በአፈር መሸርሸር ምክንያት የተጎዱና የተራቆቱ መሬቶችን የሚያሳይ በምስል የተደገፈ የጥናት ጽሑፍ በተመራማሪዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የዓለም ውኃ አዘል መሬቶች ቀን በየዓመቱ እ.ኤ.አ የካቲት 2 የውኃ አካላት ለምድራችንና ለሰዎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ለማስገንዘብ የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 90 በመቶ የሚሆኑ የዓለማችን ውኃ አዘል መሬቶች እ.ኤ.አ ከ1700 ጀምሮ መቀነስ በመጀመራቸው ውኃ አዘል መሬቶችን ከደኖች ይልቅ በ3 እጥፍ በፈጠነ ሁኔታ እያጣን እንደመጣን ጥናቶች እንደሚያመለክቱም ገልጸዋል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ ገለጻ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የትምህርት ፕሮግራሞችን ከመጀመሪያ እስከ 3 ዲግሪ በመስጠት ላይ ሲሆን ከፍተኛ ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪዎችን እንዲሁም በሚገባ የተቋቋሙ የብዝሃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ የልኅቀት ማዕከላትን በመክፈት እየተንቀሳቀሰ ላይ ይገኛል፡፡

የ‹‹Ethio-Wetlands and Natural Resources›› ግብረ ሠናይ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አፈወርቅ ኃይሉ በበኩላቸው ድርጅታቸው ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ዘርፎች መካከል በዋናነት ውኃ አዘል መሬቶች ላይ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በዓለም አቀፉ የውኃ ስምምነት መሠረት ለረዥም ጊዜ ውኃ የሚተኛባቸው መሬቶች ማለትም ሐይቆችን፣ ረግረግ መሬቶችን፣ የውኃ ዳርቻዎችንና ጨፌዎችን ያካትታል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ አካባቢ የሚገኙት ዓባያና ጫሞ ሐይቆች ከተፋሰሱ ታጥቦ በሚወርደው አፈር ምክንያት በተለይ ዓባያ ሐይቅ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረው በመሆኑም ሐይቆቹን ለመታደግ ከዩኒቨርሲቲውና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ መፍትሔ ለመስጠትና ዓለም አቀፉን በዓል በጋራ ለማክበር ፕሮግሙ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ ፕሮግራም ዳይሬክተር ወ/ሮ ሸዋዬ ደርብ በውኃ አዘል መሬት አጠባበቅ፣ ግብርና፣ ደንና አካባቢ ጥበቃ፣ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ማሰራጨት፣ ንግድና ሥራ ፈጠራ በተለይም ተዘዋዋሪ ብድር ማመቻቸት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመከላከል ችግኞችን በማፍላት ማሰራጨት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ንጹሕ ውኃ እንዲያገኙ ማመቻቸት፣ በደረቅ ወራት በውኃ እጥረት ለሚቸገሩ ሰዎች አነስተኛ የመስኖ ሥራ መሥራትና ሥልጠናዎችን መስጠት ድርጅታቸው ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ት/ክፍል መምህርና የ3 ዲግሪ ጥናታቸውን በአፈር መሸርሸርና በቦረቦር ላይ እየሠሩ የሚገኙት አቶ ልዑልሰገድ በላይነህ በዓባያ ሐይቅ ተፋሰስ አካባቢው በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑና የመሬቱ ተዳፋትነት በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የአፈር መሸርሸር እንዲፈጠር መንስኤ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በተለይ ከ1970ዎቹ ጀምሮ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አካባቢውን በከፍተኛ ሁኔታ ለአፈር መሸርሸር ተጋላጭ እያደረገውና እየጎዳው እንደመጣም ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ ተሳታፊዎች በምዕራብ ዓባያ ወረዳ አልጌ ቀበሌ ከረዥም ዓመት በፊት በዓባያ ሐይቅ አካባቢ የነበረው ውኃ አዘል መሬት ምን እንደሚመስልና በደለል አፈር የተነሳ በሐይቁና በዙሪያው የሚገኙ የውኃ አካላት እንዴት እንደተጎዱ እንዲሁም በምዕራብ ዓባያ ወረዳ የሞረዴ ቀበሌ የአካባቢው ስነ ምኅዳር ባለመጠበቁ ምክንያት የአፈር መሸርሸር አካባቢውን እንዴት እንዳራቆተው ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

ከ‹‹Menschen fur Menschen Switzerland››፣ ‹‹Co-operative Development Foundation of Canada››፣ ‹‹Ethio-Wetlands and Natural Resources››፣ ከኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ ደንና የዱር እንስሳት እንክብካቤ፣ ከጋሞ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ፣ ከጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ፣ ከጋሞ ዞን ፍትሕ መምሪያ፣ ከጋሞ ዞን ፋይናንስ መምሪያ እና ከሌሎችም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተወጣጡ ተጋባዥ እንግዶች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪዎች በውይይቱ ታድመዋል፡፡

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት