Print

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአራቱም ፋከልቲዎች ከተወጣጡ የ2015 ዓ/ም የኢንስቲትዩቱ ተመራቂ ተማሪዎች ተወካዮች ጋር የመውጫ ፈተና ቅድመ ዝግጀትን በተመለከተ መጋቢት 15/2015 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም በመውጫ ፈተና ዙሪያ ፋከልቲዎች በየደረጃቸው የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን፣ ናሙና ጥያቄዎችን እያዘጋጁና ተማሪዎች በሥነ-ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ እየሠሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው ውይይቱ በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫ ለመያዝ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ የመውጫ ፈተናው ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ከመጀመሪያ ዓመት እስከ መጨረሻ ዓመት ከወሰዱት ኮርሶች መካከል ከ15 ዋና ኮርሶች የሚዘጋጅ እንደሆነም ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ በፈተናው ዙሪያ መምህራን ተማሪዎችን ለማገዝ በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ቦጋለ ተማሪዎች ከመምህራን ጋር በመናበብና የክለሳ መርሃ-ግብሮችን በመከታተል እንዲሁም የናሙና ጥያቄዎችን በመሥራት ለፈተናው ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የሃይድሮሊክስና ውኃ ሀብት ምኅንድስና ፋከልቲ ዲን ዶ/ር ኤልያስ ገበየሁ በበኩላችው በፋከልቲያቸው በሚገኙ የተማሪ ተወካዮች ጋር ውይይት በማድረግ ፈተናው የሚዳስሳቸውን 15 ኮርሶች ዝርዝር የማሳወቅ ሥራ እንደተሠራ አመላክተዋል፡፡ በቀጣይ የክለሳ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችሉ ቁሳቁሶችና ናሙና ጥያቄዎች ዝግጅት የተጠናቀቁ በመሆናቸው ከመጋቢት 22/2015 ዓ/ም ጀምሮ የክለሳ ትምህርቱን እንደ ፋከልቲ መስጠት እንደሚጀመር ዲኑ ጠቁመዋል፡፡

የውኃ ሀብትና መስኖ ምኅንድስና ፋከልቲ የ5 ዓመት ተመራቂ ተማሪ እንደገና አበበ ውይይቱ ስለ መውጫ ፈተናው አጠቃላይ ሁኔታዎች ግንዛቤ የፈጠረለት መሆኑን ገልጾ ፈተናው የሚሰጥበት ጊዜ የቀረበ በመሆኑ የተዘጋጁ የትምህርት ቁሳቁሶች ለተማሪ በቶሎ የሚደርሱበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቋል፡፡

በውይይቱ የኢንስቲትዩቱ ሳይቲፊክ ዳሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያምን ጨምሮ የአራቱም ፋከልቲዎች ዲኖችና ተመራቂ ተማሪዎች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት