Print

ለአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራንና ተመራማሪዎች በዲጂታል ፕሮግራሚንግ፣ ሞዴሊንግ እና የመረጃ አጠቃቀም ዙሪያ ከሰኔ 3 - 5/2015 ዓ/ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የውሃ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል ዳጋሎ ሥልጠናው ቀጣይነት ያለው የውሃ ምንጮች ልማት፣ አጠቃቀምና አያያዝ ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በዋናነት ለመምህራንና ለተመራማሪዎች፣ 2ኛና 3ኛ ዲግሪያቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ለምርምሮቻቸው ከርቀት የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በፍጥነት አግኝተው ጥናታቸውን ማካሄድ እንደሚያስችላቸው ዶ/ር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ደመላሽ ወንድምአገኘሁ ሥልጠናው በውጭ ሀገር በዘርፉ  በማስተማር እና የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በሚገኙ ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች መሰጠቱ ወደ ዲጂታል የተቀየሩ መረጃዎችን ከርቀት መሰብሰብ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርምርና የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማሳለጥ አስተዋጽኦው የጎላ ከመሆኑም ባለፈ  የውሃና የግብርናውን ዘርፍ በማዘመኑ ሂደት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው  ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ መምህራንና ተመራማሪዎች በተለይ መሰል የዲጂታል ሥልጠናዎችን መውሰዳቸው በመረጃ ዕጥረት ምክንያት ተጀምረው የተቋረጡ ምርምሮችን የማስቀጠል ዕድልም እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ባልደረባ እና በኔዘርላንድ አይ.ኤች.ኢ ደልፍት የውሃ ትምህርት ተቋም “IHE Delft Institute for Water Education” መምህር  ዶ/ር አበበ ደምሴ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች በአብዛኛው ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተቀየሩ ያሉ በመሆኑ የሚሰጠውን አገልግሎት ቅልጥፍናና ፍጥነት ለመጨመር፣ መረጃዎችን በዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ወደ ዲጂታል የተቀየሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን በመጠቀም በመሬትና ውሃ ዙሪያ መረጃዎችን በጥልቀት ለመረዳት እንዲቻል ሥልጠናው የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ዶ/ር አበበ አክለውም ሥልጠናው በተለይ የ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪዎቻቸውን እየሠሩ ለሚገኙ፣ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ተግባራትን ለሚያከናውኑ መምህራንና ተመራማሪዎች ወደ ዲጂታል የተቀየሩ የፕሮግራሚንግ እና ሞዴሊንግ መረጃዎችን አጠቃቀም አቅም ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኔዘርላንድ ደልፊት የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ/Delft University of Technology/ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ሌላኛው አሠልጣኝ ዕጩ ዶ/ር በዳሳ ረጋሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ማሽን ትምህርቶች አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (Artificial Intelligence/AI)ን የመጠቀም ሁኔታ እያደገ መጥቷል፡፡ እንደ አሠልጣኙ ማሽን ለርኒንግ/Machine Learning/ እና ዲፕ ለርኒንግ/Deep Learning/ በመባል የሚታወቁ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂዎች በኮምፒውተር ሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና ጤና ዘርፎች ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ከመምጣቱም ባሻገር ጠቀሜታቸውም የጎላ ሲሆን የዘርፉ ዕውቀት ለአየር ንብረት፣ ለውሃ ምንጭና መስኖ በየጊዜው የሚያስፈልገውን መጠን ለማሻሻልና ለመተንበይ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አሠልጣኙ ጠቁመዋል፡፡

የሳተላይት መረጃዎችን በውሃና መሬት አጠቃቀም ላይ የማግኘትና መሰብሰብ ሁኔታ፣ የተለያዩ መረጃዎችን ማውጣት እንዲሁም ችግሮች ሲከሰቱ መለየትና ወደ መፍትሄ መቀየር የሚቻልባቸው መንገዶች ሥልጠናው ትኩረት የሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በሥልጠናው  የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን፣ ተመራማሪዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት