Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ/Justice for All Prison Fellowship Ethiopia/ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በወንጀል ምርመራና ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ላይ ለደቡብ ክልል መርማሪ ፖሊሶች ከሰኔ 9-10/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ የሴቶችና ሕጻናት መብት አማካሪ ወ/ሮ ሃና ኪዳኔ የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክተው እንደተናገሩት ጀስቲስ ፎር ኦል ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ውስጥ ፆታን መሠረት አድርገው የሚደርሱ ጥቃቶችን በየትኛውም አካባቢ ለመቀነስ፣ ጥቃት ደርሶባቸው ፍትሕ ፈልገው የሚመጡ ሴቶች ለደረሰባቸው ጥቃት ትክክለኛ ፍትሕ እንዲያገኙና የፍትሕ አካላት ሥራ የተቀላጠፈና ውጤታማ እንዲሆን በማገዝ አቅማቸውን ማሳደግ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ውድቅ የሚሆኑት በመርማሪ ፖሊሶችና ዐቃቢያን ሕጎች ዘንድ በመዝገብ አደረጃጀት እና ማስረጃ አሰባሰብ ረገድ ባሉ ጉድለቶች ምክንያት መሆኑን አመላክተው ችግሩንም ለመቅረፍ የመርማሪ ፖሊሶችን ልምድ፣ ለሥራቸው እንቅፋት የሚሆኑባቸውን ጉዳዮች በመለየት የማገዝ የመደገፍና አቅማቸውን የማሻሻል ሥራዎች እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሮ ሃና አክለውም በቀጣይ ሠልጣኞች ቀድሞ የነበራቸውን አሠራር ከሥልጠናው ካገኙት ግንዛቤ ጋር በማነጻጸርና ራሳቸውን በመገምገም ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚጠበቅባቸው እንዲሁም ያገኙትን ዕውቀት በተግባር በመፈጸም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሊከላከሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም በተጨባጭ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለይቶ በመሥራት  ለማኅበረሰቡ እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ በርገኔ ይስሐቅ በበኩላቸው የወንጀል ምርመራ ሂደት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ሰፊ ክፍተቶች የሚታዩበት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ በርገኔ በተለይ በየአካባቢያችን እየተስተዋሉ ያሉ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን አስመልክቶ በምርመራው ላይ የተሠማሩ መርማሪ አካላት በሥልጠናው እንዲሳተፉ መደረጉ በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት በመቅረፍ ብሎም በፍርድ ቤቶች የተያዙ እንዲሁም የሥልጠናው ተሳታፊዎች በእጃቸው ላይ ያሉ ጉዳዮችን በአፋጣኝ እና በትክክል ለውሳኔ እንዲበቁ በማድረግ የተጣለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት እንዲወጡ አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ፍትሕ ለአንድ ሀገር ዕድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ የፍትሕ ይዘት፣ ጥራትና ዓይነት፣ አደረጃጀት፣ አወቃቀርና አመቺነት፣ የፍትሕ መተግበሪያ ዘዴና ስትራቴጂ እንዲሁም አጠቃላይ ሥርዓተ ፍትሕ ግልጽ ሊሆንና በተገቢው መንገድ ሊመራ ይገባል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርቲውም በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፉ በፍትሕ ዙሪያ የሚያደርገውን ተልዕኮ ከመቼውም በላይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው በወንጀል ምርመራ ላይ በመሠማራት እውነትን ፍለጋ ለሚተጉ ሙያተኞች አክብሮት እንዳላቸውም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በወንጀል ምርመራና የተከሰሱ ሰዎች መብት እንዲሁም የወጣት ጥፋተኞች እና የታራሚዎች መብት በሚል ርዕስ ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ ሲያከናውኑት የነበረውን የምርምር ፕሮጀክት ውጤት መሠረት አድርገው ሥልጠና የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ አቶ ዳግም ወንድሙ ውጤታማ የወንጀል ሥርዓትን ለማስፈን ሚዛናዊነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው የወንጀል ምርመራ ሂደት አንድን ጉዳይ ብቻ የሚወስን ሳይሆን አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለውን የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት የሚወስን፣ የሚያስተካክል መልካም ካልሆነ ደግሞ የሚጎዳ ውጤት ይዞ የሚመጣ በመሆኑ መርማሪ ፖሊሶች በወንጀል ምርመራ ሂደት ላይ የሚያሳዩት ብርቱ ትጋትና ቸልተኝነት በወንጀል ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

መ/ር ዳግም አክለውም የወንጀል ምርመራ ሂደቱ ሕጉን ያልተከተለና የተከሰሱና የተያዙ ሰዎችን መብት የሚጥስ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በዐቃቢያን ሕጎችና በፖሊስ መካከል ትብብር ያለመኖር፣ ፖሊሶችንና መርማሪ ፖሊሶችን ያለመቆጣጠር፣ ጥሰቶች ሲፈጸሙ ተጠያቂነት ያለመኖር፣ የክሂሎትና የዕውቀት ችግሮች እንዲሁም የደቦ ፍርድ የወንጀል ምርመራ ተግዳሮቶች ሆነው በጥናቱ መለየታቸውን አመላክተዋል፡፡ በተጨማሪም ቅድመ ፍረጃ፣ ተከሳሽ ወይም ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ለረጅም ጊዜ ማቆየት፣ በድብደባና በኃይል ተጠርጣሪው እንዲያምን ማድረግ፣ የታሰረበትን ምክንያት አለማሳወቅ፣ የወንጀል ምርመራ ሂደቱ የተከሳሽን ግላዊነት ያላከበረ መሆኑ ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች ሆነው በምርምሩ ሂደት መስተዋላቸውን መ/ር ዳግም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በማስረጃና ምርምር መርሆዎች እና እየታዩ ባሉ ክፍተቶች ላይ ሥልጠና የሰጡት በጋሞ ዞን ፍትህ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች አስተባባሪ ዐቃቢ ሕግ አቶ ጤናሁን ጨርቆስ የወንጀል ምርመራ በራሱ ግብ ሳይሆን የግብ ማሳኪያ ሂደት ሲሆን የሕጉ ዓላማም ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የሀገሪቱን፣ የመንግሥትን፣ የሕዝብንና የነዋሪዎችን ሠላምና ደኅንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ጤናሁን አክለውም ማስረጃ ከአንድ የወንጀል ድርጊት ጋር ግንኙነት ያለው የወንጀል አድራጊውን ሁኔታ ለመለየት፣ አጥፊዎች  ለፈጸሙት ሕገ ወጥ ተግባር በሕግ  እንዲጠየቁ  ለማድረግ፣ ትክክለኛው የወንጀል አጥፊ ላይ ለመድረስ፣ በፍትሕ ሥርዓት አሠራር ውስጥ ጊዜንና ገንዘብን ለመቆጠብ እንደሚጠቅም እንዲሁም የሐሰት ክስንና ምስክርነትን ለመቆጣጠር እና የተሳሳተ ውሳኔ እንዳይወሰን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ፖሊሶችና ዐቃቢያን ሕጎች በአንድነት በመናበብ ማስረጃዎችን በጥንቃቄና በአግባቡ በመቀበል ምርመራዎችን በስልታዊነት በመምራት ውጤታማ ልናደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የሚደርስባቸው ሰዎች ከጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን አስመልክቶ ሥልጠና የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መ/ር ረ/ፕ ድንቅዓለም ጌታሁን  በ2008 ዓ/ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ጥናት ከ5,800 ሴቶች መካከል 26%ቱ ፆታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ሲሆን ከነዚህም 80%ቱ ምንም ዓይነት የሕግና የጤና አገልግሎት የማያገኙና ለሌላ ሰውም የደረሰባቸውን ጥቃት የማይነግሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡  በመሆኑም ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሰዎችን ከተለያዩና ውስብስብ ከሆኑ ችግሮች ለመታደግ በ72 ሰዓታት ውስጥ የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ መርማሪ ፖሊሶችና በየደረጃው ያሉ የአስተዳደርና የማኅበረሰብ አካላት እንዲሁም ቤተሰብ ተጠቂዋን በቅድሚያ ወደ ጤና ተቋም ሊወስዷት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በሚሠሩት ሥራ ላይ ያለውን ክፍተት ለይቶ በማውጣትና አቅጣጫዎችን በማሳየት በቀጣይ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አገልግሎቶችን በቁርጠኝነት እንዲሰጡ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሥልጠናው በኋላም በምርመራ ተግባር ላይ ሊውሉ የሚገቡ ጠቃሚ መረጃዎችን በመውሰድና ሕግን መሠረት በማድረግ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የዜጎችን መብት ጠብቀው የምርመራውን ዓላማ ማሳካት እንዳለባቸው የተማሩበት መሆኑን አክለዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት