Print

በሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ‹‹ማሠልጠን፣ ማብቃትና መሸለም›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በ‹‹ብሩህ ኢትዮጵያ 2015 የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር›› ላይ የተሳተፉ ተማሪ ሰርካለም ደሳለኝ እና አልአዛር ቅጣው አሸነፉ፡፡ ከውድድር መልስም  ሰኔ 20/2015 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የእንኳን ደስ አላችሁ አቀባበል ተደርጓል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥራና ክሂሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት የሥራ ፈጠራ እንደ ሀገር ብልጽግናንና ዘላቂ ልማትን ለማስቀጠል ከማስቻሉም በላይ በርካታ ወጣቶችን በማሳተፍ ሁሉን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉ በርካታ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት ተገቢ በመሆኑ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡  በውድድሩም  ችግር ፈቺ የሆኑ ሃሳቦች የተገኙበት፣ ወደ ውጭ የሚላኩና የሚገቡ ምርቶች የተለዩበት እንዲሁም የናሙና ሙከራዎች ማየት የተቻለበት እና አካል ጉዳተኝነትን እንደ ልዩ ችሎታ ማሳየት የተቻለበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለብዙዎች ተስፋና ለሀገር አለኝታ የሆኑ በርካታ እህት ኩባንያዎችን ማፍራት እንደሚያስችል አመላክተዋል፡፡ ሚኒስትሯ አክለውም ጀማሪዎች ሃሳባቸውን ከዳር ለማድረስ ጠንክሮ በመሥራት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጽናት መወጣት እንዳለባቸውና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትስስር መሥራት እንደሚገባቸው ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ በብሩህ ኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ላይ ሲሳተፍ የቆየ ሲሆን በዘንድሮው ውድድርም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተደረገ ጥሪ መነሻነት ቀደም ሲል በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከተወዳደሩ ተማሪዎች 10 ተወዳዳሪዎች ተመልምለው ቀርበዋል፡፡ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል ሁለቱ ከውድድሩ ፍጻሜ ደርሰው ከ50ዎቹ ውስጥ በመግባት እያንዳንዳቸው 260,000 (ሁለት መቶ ስልሳ) ሺህ ብር ተሸላሚ ሲሆኑ ለዩኒቨርሲቲውም የዕውቅና ምስክር ወረቀት መበርከቱን ዶ/ር ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በውድድሩ ከ8 ክልሎች፣ ከ2 ከተማ አስተዳደሮች እና ከ14 ዩኒቨርሲቲዎች 200 የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች የተሳተፉ ሲሆን ተወዳዳሪዎቹን ለውድድሩ ብቁ ለማድረግ ለ20 ቀናት ሥልጠና እንዲሁም ለሦስት ዙሮች ማጣሪያ ተከናውኗል፡፡ ተሸላሚዎቹ በፍጻሜ ውድድሩ የተወሰነ የናሙና ምርት ማቅረባቸውን የገለጹት ዶ/ር ወንድወሰን አሸናፊነታቸው የበለጠ የሚረጋገጠው የፈጠራ ውጤቶቹ ወደ ገበያ ገብተው አዋጭነታቸው በተግባር ሲረጋገጥና ለራሳቸውና ለሌላው ማኅብረሰብ የሥራ ዕድል መፍጠር ሲችል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ለዚህም ተማሪዎቹ ሃሳባቸውን ወደ መሬት እንዲያወርዱ ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪና አጋር ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር የራሳቸውን ካፒታል እንዲፈጥሩ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የማዕከሉ የሥልጠና ክፍል አስተባባሪ መ/ር አበበ ዘየደ በበኩላቸው በስድስቱም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ተማሪዎች በማወዳደር የተሻለ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወደ ሀገር አቀፍ ውድድር እንደሚልኩ ገልጸው የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ከአዕምሮ ወደ ወረቀት የሚወለድና ተግባራዊ ሲሆን የሚያድግ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በአቀባበል መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የተገኘው ተስፋ ሰጪ ድል የተማሪዎቹና የመምህራኑ የጋራ ልፋት ውጤት መሆኑን ጠቅሰው ለቢዝነስና ኢኮኖሚስ ኮሌጅ፣ በዘርፉ ትኩረት አድርገው ለሠሩ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ውጤቱ ለተከታይ ተማሪዎች ጥሩ መነሳሳትን እንደሚፈጥርና የሥራ ፈጠራ ሃሳቦቹ እውን እስኪሆኑ በመከታተል መደገፍ ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከሙዝ፣ ከአቦካዶ እና መሰል ተረፈ ምርቶች የሚመረት የእንስሳት መኖ በማዘጋጀት በገበያ ላይ ያለውን የከብቶች መኖ ውድነት ለመቅረፍ የፈጠራ ሃሳብ ያቀረበችው የ2ኛ ዓመት የሶፍትዌር ምኅንድስና ተማሪ ሰርካለም ደለለኝ አሸናፊ በመሆኗ መደሰትዋን ገልጻለች፡፡ በቀላሉ በአካባቢው ከሚገኙ ተረፈ ምርቶች የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ያለው የእንስሳት መኖ በማዘጋጀት በቅናሽ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ አስባ መነሳቷን ተማሪዋ ተናግራለች፡፡ ተማሪ ሰርካለም ለሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል አባላትና ለሌሎችም ለሥራዋ ስኬት ከጎንዋ ለነበሩ ሁሉ ምስጋናዋን አቅርባ የፈጠራ ሃሳቧን ወደ ተግባር ለመቀየር እንደምትተጋ ገልጻለች፡፡

 ሌላኛው ተሸላሚ የ4ኛ ዓመት የአካውንቲንግና ፋይናንስ ተማሪ አልአዛር ቅጣው ማርከር የማምረት የፈጠራ ሥራ ይዞ የቀረበ ሲሆን ከውጭ የሚገቡ ማርከሮች አገልግሎታቸው በሚገዙበት ወጪ ልክ አለመሆኑ ለፈጠራ ሥራው እንዳነሳሳው ተናግሯል፡፡ በፈጠራ ሥራው ከፕላስቲክ የሚመረተውን ማርከር በወረቀት መተካት እንደቻለና የተለያዩ ኬሚካሎችና አዲስ ፈጠራ ታክሎበት የራሱ የቀለም ማስቀመጫ ያለው በፑሊንግ ሲስተም እየተሞላ የሚሠራ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

ተማሪ አልአዛር ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችና ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን መተካት ላይ ቢያተኩሩ የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ሀገርን ለመለወጥ የጎላ ድርሻ ስላላቸው መደገፍና ማብቃት ላይ እንደ ሀገር የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተማሪው ጠቁሟል፡፡

በውድድር ሂደቱ ጠንካራ ልምድ ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ልምዳቸውን ያጋሩ ሲሆን በሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር እንደተገለጸው ከተወዳዳሪዎቹ መካከል 70ዎቹ የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የብድር አገልግሎትና ሌሎች ድጋፎች የሚመቻችላቸው ይሆናል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት