Print

በአዲሱ የፌዴራል መንግሥት መዋቅራዊ አደረጃጀት ለውጥ መሠረት የአስተዳደር ሠራተኞችን ድልደላ ለመፈጸም የየሥራ ክፍሉ ተወካይ ሠራተኞች በተገኙበት ሰኔ 26/2015 ዓ/ም የድልደላና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች የሠራተኛ ተወካይ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደገለጹት ከትምህርት ሚኒስቴር በተላከው መዋቅር መሠረት የሠራተኞችን ድልደላ ተግባራዊ ለማድረግ በመመሪያው መሠረት የደልዳይ ኮሚቴ ምርጫ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ደልዳይ ኮሚቴው ሲዋቀር አባላቱ ሁሉንም ሠራተኛ የሚወክሉ፣ ሙያቸውን የሚያከብሩ፣ በሥራ አፈጻጸምና በሥነ-ምግባር ከፍተኛ ውጤት ያላቸው፣ ታማኝና ምሥጢር ጠባቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ም/ፕሬዝደንቷ አሳስበዋል፡፡

የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ የሠራተኞችን ድልድል በወጥነት ለማከናወን ረቂቅ የድልድል መመሪያ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተዘጋጅቶ ውይይት የተደረገ መሆኑን፣ ኅዳር 20/2014 ዓ/ም በኮሚሽኑ ማኔጅመንት ኮሚቴ ታይቶ መጽደቁንና ለፍትሕ ሚኒስቴር በድጋሚ ተልኮ በመመሪያ ቁጥር 859/2014 የተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ከሠራተኛ ድልድል ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የሠራተኞች የድልድል ኮሚቴ ማዋቀር ሲሆን ሠራተኛውን በሚመለከት ማንኛውም ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ የሠራተኛ ተወካዮችን መምረጥ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም በመመሪያው አንቀጽ 8 እና 9 መሠረት አንድ ሰብሳቢ፣ አንድ አባልና አንድ ጸሐፊ በዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ የሚወከል ሲሆን ሦስት የሠራተኛ ተወካዮች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ከሠራተኞች በሚሰጡ ጥቆማዎችና የድጋፍ ድምጾች ይመረጣሉ፡፡ ተወካዮቹ ከደልዳይ ኮሚቴው ጋር በጋራ የሚሠሩ ሲሆን በመመሪያው መሠረት ለደልዳይ ኮሚቴውና ለሠራተኛው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ገለጻ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዕለቱ በተደረገው ምርጫ ለደልዳይ ኮሚቴ የሠራተኛ ተወካይነት ስድስት ጥቆማዎች እንዲሁም ለቅሬታ ሰሚ የሠራተኛ ተወካይነት አራት ጥቆማዎች ተሰጥተው ሦስት የደልዳይ ኮሚቴ የሠራተኛ ተወካዮችና ሁለት ቅሬታ ሰሚ የሠራተኛ ተወካዮች በአብላጫ ድምጽ ተመርጠዋል፡፡ ለደልዳይ ኮሚቴ አቶ መሠለ እሸቴ በ146 ድምጽ፣ አቶ ታምሩ ካሣ በ99 ድምጽ እና ወ/ሮ ስንታየሁ እጅጉ በ82 ድምጽ የሠራተኛ ተወካይ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ለቅሬታ ሰሚ የሠራተኛ ተወካይ አቶ ዘማቹ ዘካሪያስ በ142 ድምጽ እና ወ/ሮ ጥሩነሽ ቶቤ በ120 ድምጽ ተመራጭ ሆነዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት