Print

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ከጋሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን  ቴክኖሎጂ መምሪያ ጋር በመተባበር ከዞኑ  14 ወረዳዎች፣ ስድስት የከተማ አስተዳደሮችና አምስት የግል ማኅበራት ለተወጣጡ የICT እና የቢሮ ማሽን ጥገና ባለሙያዎች ከሰኔ 12- 16/2015 ዓ/ም የቢሮ ማሽን ጥገና ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ መሰል ሥልጠናዎች የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረው ዞኑን በሙያም በሰው ሀብትም ለማገልገል የባለሙያዎችን ዕውቀት በማጎልበት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ሙሉጌታ እንደገለጹት በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የምርምር ውጤቶች የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉና ተግባር ተኮር እንዲሆኑ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን ሥልጠናው በቢሮ ማሽኖች ላይ ችግር ሲገጥማቸው ባለሙያዎች  ችግሩን እየፈቱ ሥራዎችን እንዲያሳኩ ያደርጋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ አስተባባሪና አሠልጣኝ መ/ር ጌታቸው ተዋቸው እንደገለጹት ሥልጠናው ከሀርድዌር/Hardware/ እና ሶፍትዌር/Software/ ጥገና ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር እንዴት በቀላሉ መፍታት እንደሚቻል የሚያሳይ፣ የቢሮ ማሽን ጥገና ክሂሎታቸውን የሚያዳብር እንዲሁም የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ዕውቀት ክፍተታቸውን በመቅረፍ ብቁ ባለሙያ የሚያደርጋቸው ነው፡፡

የጋሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ካቦ ከተማ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው ተልእኮ አንዱ ማኅበረሰብን ማገልገል ስለሆነ ባቀረብነው ጥያቄ መሠረት ሥልጠናው ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ሥልጠናው ባለሙያዎችን በማብቃትና ክሂሎታቸውን በማዳበር የቢሮ ማሽን ጥገናን አስመልክቶ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍና መንግሥት ለጥገና የሚያወጣውን አላስፈላጊ ወጪ ለማዳን የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው የክሂሎት ክፍተታችንን እንድናይና እንድንረዳ ትልቅ ዕድል የፈጠረልን ሲሆን በሚቀጥለው ጊዜ የተሰጠንን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ እንድንወጣ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ የሥልጠናው ጊዜ ረዘም አንዲልና ዕድሉን ላላገኙ ባለሙያዎችም እንዲዘጋጅ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በሥልጠናው መክፈቻ መርሃ ግብር የአርባ ምንጭ ቴክናሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር፣ የኢንስቲትዩቱ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የጋሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ፣ የጋሞ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ እንዲሁም ሠልጣኞች የተገኙ ሲሆን በሥልጠናው መጨረሻ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት