Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል አዘጋጅነት በሁሉም ካምፓስ ተማሪዎች መካከል ሲደረግ የቆየው የ2015 ዓ/ም 2ኛ ዙር የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ሰኔ 16/ 2015 ዓ/ም ተጠናቋል፡፡ በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ስድስት የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳቦች ቀርበው ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት እንዲሁም ለቀሪዎቹ ተወዳዳሪዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡ የተሻሻለ የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን፣ ዘመናዊ ጡብ ማምረቻ፣ ከአፈር ውጭ ውሃን በመጠቀም የጓሮ አትክልቶችን ማምረትና ከሙዝ ግንድ ወረቀት ማምረት ከቀረቡ የፈጠራ ሥራ ሃሳቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በትምህርት የሰው ልጅ አመለካከቱን፣ ዕውቀትና ክሂሎቱን እንደሚያሳድግ ጠቅሰው ያላቸውን ጊዜ ተጠቅመው በትምህርት  ያገኙትን ዕውቀት ወደ ፈጠራ ሃሳብ መቀየር መቻላቸው የፈጠራ ሃሳብ ባለቤት ስለመሆናቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ተወዳዳሪዎች ከዳኞች ያገኙትን አስተያየት በመጠቀም ሥራዎቻቸውን ወደ መሬት ለማውረድ ጠንክረው መሥራት እንደሚገባቸው ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡ ለዘርፉ መጠናከር የበኩላቸውን ተሳትፎ ላደረጉ  የሥራ ክፍሎችና መምህራንም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ተወዳዳሪዎቹ በቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት ዙሪያ ሥልጠና መውሰዳቸውንና ድጋፍ ሲደረግላቸው እንደነበር አስታውሰው ተማሪዎች ከሚማሩት የቀለም ትምህርት በተጨማሪ የሥራ ፈጠራ ክሂሎታቸው እንዲዳብር ታልሞ መርሃ ግብሩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም እንደ ሀገር የሥራ አጥነት መጨመር ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ገልጸው ይህን ለመቅረፍ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ግንዛቤ ማዳበርና በትምህርት የሚገኝ ዕውቀትን ከተግባር ልምድ ጋር በማጣመር ወደ ፈጠራ ሃሳብ እንዲያመሩ ዕድሉን ማመቻቸት ይገባል ብለዋል፡፡ ውደድሩ በአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር ይረዳል ያሉት ዳይሬክተሩ በቀጣይ በሚኖራቸው የሥራ ጊዜ ሙያዊና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች ላይ ያለንን አስተዋጽኦ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

በውደድሩ 1ኛ የወጣው የሜካኒካል ምኅንድስና ተማሪ እስራኤል ኃይሉ ያቀረበው የተሻሻለ የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን ንድፈ ሃሳብ ጊዜ ቆጣቢ፣ የእናቶችን ድካም የሚያስቀርና በቅናሽ ዋጋ ማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ተናግሯል፡፡ ተማሪ እስራኤል ወድድሩ በርካታ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶችን ወደ ሕዝቡ እንዲወጡ ዕድል የሚፈጥርና ይህም የፈጠራ ሐሳብን ወደ ተግባር ለመቀየር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በውድደሩ 2ኛ የወጣው የሜካኒካል ምኅንድስና ተማሪ ሱሌይማን አበበ ብሎኬትን የሚተካ ዘመናዊ ጡብ ማምረት የፈጠራ ሃሳቡ ሲሆን የብሎኬትና የሲሚንቶ ዋጋ መናር ወደ ፈጠራ ሃሳቡ እንዳመራው ተናግሯል፡፡ ለጡብ መሥሪያነት የሚያገለግለውን አፈር በቀላሉ በአቅራቢያው ማግኘት መቻሉ ለፈጠራ ሃሳቡ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረለት ያወሳው ተማሪ ሱሌይማን የፈጠራ ሃሳቡ ለሀገሪቱ የግንባታ ዘርፍ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተስፋውን ገልጿል፡፡

አክሎም ለቀጣይ በተግባር የታገዘ ዕውቀት እንዲኖር የቤተ-ሙከራ ማዕከል ማቋቋም ላይ ተጠናክሮ ቢሠራ በርካታ ለሀገር የሚጠቅሙ ወጣቶችን ማፍራት እንደሚያስችል ተማሪ ሱሌይማን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት