Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ሐምሌ 10/2015 ዓ/ም በቤሬ ተፋሰስ ላይ ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትክል በ5ው ዙር የአረንጓዴ አሻራና በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ላይ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለመርሃ ግብሩ ባሉት ዘጠኝ የችግኝ ጣቢያዎች ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኞችን አዘጋጅቶ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች እየተሰራጨ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ከሚሠራባቸው መስኮች መካከል ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት አራት ዓመታት ከተተከሉ ችግኖች መካከል 90 በመቶ ያህሉ መጽደቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በማኅበረሰብ ጉድኝት በኩል ዓመቱን ሙሉ አስፈላጊውን እንክብካቤ የሚያደርግ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ዳምጠው በዘንድሮው ዓመት እንደ ሀገር ‹‹ነገን ዛሬ እንትከል!›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ያደረገው የነቃ ተሳትፎ አስደሳች ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ችግኞችን የማፍላትና ለማኅበረሰቡ የማሰራጨት፣ የተፈጥሮ ደኖችን የመጠበቅ እና የተጎዱ ሥነ ምኅዳሮችን መልሶ የማልማት ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዩኒቨርሲቲው በጋሞና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም በደራሼ ልዩ ወረዳ ባቋቋማቸው ዘጠኝ ችግኝ ጣቢያዎች አማካኝነት የፍራፍሬ እና ለአካባቢ ጥበቃና ለከተማ ውበት የሚውሉ ችግኞችን በማፍላት በየዓመቱ ለማኅበረሰቡ የሚያሰራጭ ሲሆን ዘንድሮም ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኞችን በማፍላት እያሰራጨ ይገኛል ብለዋል፡፡ በምዕራብ አባያ ወረዳ ከፉራ እስከ ሃመሳ ወንዝ ድረስ ያለውን ጥብቅ ደን ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመሆን ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተክሉ ላለፉት አራት ዓመታት የቤሬ ተፋሰስን መልሶ ለማልማት እየተከናወኑ ያሉ አካላዊና ሥነ ሕይወታዊ ሥራዎች በዘርፉ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መከከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቤሬ ተፋሰስ ላይ የተተከሉ ችግኞች በተደረገላቸው እንክብካቤና ጥበቃ አብዛኞቹ የጸደቁ ሲሆን በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ከ10 ሺህ በላይ ለቦታው ተስማሚ የሆኑ የወይራ፣ ወይበታ፣ ኮሬና የቆላ ቀርከሃ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ የችግኝ ተከላ ሥራው በቀጣይ በዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ቅጥር ግቢ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ተክሉ የእንክብካቤና ጥበቃ ሥራውም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በትኩረት የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቀልቦ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር አካል በመሆን አሻራቸውን በማኖራቸው በእጅጉ መደሰታቸውንና በዕለቱ በግላቸው ከ30 በላይ ችግኞችን እንደተከሉ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በተደረጉ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሰው ሀብት አስተዳደርና ል/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ በአስተያየታቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለልጆቻችን ተፈጥሮዋ የተጠበቀና ለም ሀገር ለማስረከብ የሚረዳ ተግባር በመሆኑ በተለይ ለእኛ ለእናቶች ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡ በዛሬው መርሃ ግብር በግላቸው ከ20 በላይ ችግኞችን የተከሉ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተከላው ላይ ያሳየውን የነቃ ተሳትፎ በቀጣይ ባሉ የእንክብካቤ ሥራዎች ላይ እንዲደግም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በችግኝ ተከላው ላይ ከተሳተፉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት መካከል የፌዴራል ፖሊስ ሬጅመንት 4 የ1 ሻምበል አዛዥ ም/ኢንስፔክተር ቸሬ የኔዓለም አባሎቻቸው ከሚያከናውኑት ጸጥታን የማስጠበቅ ሥራ ባሻገር ከማኅበረሰቡ ጋር በሚሠሩ መሰል የልማት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ችግኝ መትከል  ጉልህ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ተግባር በመሆኑ በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎችም እንደ ዜጋ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን  አዛዡ አመላክተዋል፡፡

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት