Print

በአዲሱ የፌዴራል መንግሥት መዋቅራዊ አደረጃጀት ለውጥ መሠረት በሠራተኞች የድልድል አፈጻጸም መመሪያ ዙሪያ በሁሉም ካምፓስ ለሚገኙ የአስተዳደር ሠራተኞች ከነሐሴ 16-19/2015 ዓ/ም ድረስ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት መድረኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ በተሻሻለው የዩኒቨርሲቲዎች መዋቅራዊ አደረጃጀት መመሪያ መሠረት የሚካሄደውን የሠራተኞች ድልደላ አስመልክቶ ሠራተኛውን ከመመሪያውና ከድልደላው አሠራር ሂደት ጋር ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ መመሪያውም  በሲቪል ሰርቪስ ተዘጋጅቶ በትምህርት ሚኒስቴር ታይቶና አስፈላጊው ማሻሻያ ተደርጎበት ከፀድቀ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መላኩን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡     

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ትምህርት ሚኒስቴር የመዋቅር ለውጡን መመሪያ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የላከ በመሆኑ አዲሱን መዋቅር ተግባራዊ ለማድረግ በመመሪያው መሠረት የደልዳይ እና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የሠራተኞችን ፋይል የማደራጀት ሥራም መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡ ወ/ሮ ታሪኳ የተመረጡት ደልዳይ ኮሚቴዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሁሉንም ሠራተኞች በማከለ ሁኔታ ታማኝና ምሥጢር ጠባቂ ሆነው ድልደላውን በጥንቃቄ እንዲያከናውኑ ያሳሰቡ ሲሆን ሠራተኛውም በመመሪያው መሠረት ያለውን የሥራ ልምድና ብቃት መሠረት በማድረግ ተገቢውን መደብ መርጦ መወዳደር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የደልዳይ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ እንደገለጹት የሠራተኞች ድልድል በወጥነት እንዲከናወን ረቂቅ የድልድል መመሪያ በሲቨል ሰርቪስ ኮሚሽን ፀድቆ በፍትሕ ሚኒስቴር በመመሪያ ቁጥር 859/2014 ተመዝግቦ የተላለፈ ሲሆን ዋና ዓላማውም አዲስ የተደራጁ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ለተሰጣቸው ተልዕኮ የሚመጥን ብቃት ያለው የሰው ኃይል ስምሪት እንዲያካሂዱ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሠራተኞች ድልድል ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የደልዳይ ኮሚቴ የሠራተኞች ተወካይ ምርጫ ማካሄድ ሲሆን ኮሚቴዎቹም በድልደላው ሂደት ሠራተኛውን በሚመለከት ማንኛውንም ጉዳይ እንደሚፈጽሙ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡   

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የደልዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አየልኝ ጎታ በበኩላቸው የሠራተኞች ድልድል የሚካሄደው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አዲስ አደረጃጀት መሠረት በነጥብ የሥራ ምዘና ዘዴ ተመዝነው ደረጃ እና የመደብ መታወቂያ ቁጥር በተሰጠባቸው የሥራ መደቦች ላይ ብቻ በመሆኑ ሠራተኞች  መደብ ምርጫ ከማድረጋቸው በፊት በሁሉም ዘርፍ ያለው መደብ የሚጠይቀውን መስፈርት በመገንዘብ በጥንቃቄ መደብ ምርጫ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም ነሐሴ 24/2015 ዓ/ም የመደብ ምርጫ ማስታወቂያ ሠሌዳ ላይ እንደሚገለጽ እንዲሁም ከመስከረም 3-9/2015 ዓ/ም የመደብ ምርጫ ቅፅ የሚሞላበት ጊዜ ሲሆን ከመስከረም 19/2015 ዓ/ም ጀምሮ ደግሞ ደልዳይ ኮሚቴው የምደባ ሥራ የሚጀምር መሆኑን አቶ አየልኝ ጠቁመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት