Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ፈጠራ፣ ልማትና ማፍለቂያ ማዕከል ከኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት /Entrepreneurship Development Institute/ ጋር በመተባበር ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ፐብሊክ ኢንተርፕሪነርሺፕ፣ ኢኖቬሽንና ሥነ ምኅዳር ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከጥቅምት 29 - ኅዳር 1/2016 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት ገቢ ማሰባሰብ፣ የሀብት አያያዝና ሀብት አጠቃቀም ጋር የቅርብ ግንኙነት ላላቸው የተቋሙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሥልጠናው መሰጠቱ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ሥልጠናው ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እየተሠራ ካለው ሥራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙት ያለው መሆኑን የጠቀሱትፕሬዝደንቱ ወደ ራስ ገዝ ለመድረስ እያንዳንዱ ግለሰብ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና የጋራ የሆነ ግንዛቤ በመያዝ የራሱን ጥረት ማከል ይገባዋል ብለዋል፡፡

እንደ ፕሬዝደንቱ የውስጥና የውጪ የገቢ ምንጮችን በማሳደግ እና ያሉ ዕድሎችን በዕቅድ አስደግፎ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ምርምርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለውጥ ማምጣት የሚቻል ሲሆን ሥልጠናው በተለይም የበላይ አመራሮች የማመቻቸት፣ የማቀናጀትና የመምራት ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ ያስችላቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ፣ ልማትና ማፍለቂያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ሥልጠናው በተለይ የከፍተኛ ትምህርትና ሌሎች የሕዝብ ተቋማት በቢዝነስ ዓለም ያለውን ትርፍ በማወቅ በእጃቸው ባለው በጀት የውስጥ አሠራርን መቅረጽ፣ ችግርን በጋራ መፍታትና የቡድን ሥራን አብሮ መሥራትን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያግዝ ታስቦ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ሀገራችን በከፍተኛ የበጀት እጥረት ውስጥ ባለችበት እንዲሁም እንደ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን ጥረት በምናደርግበት ጊዜ ላይ በመሆናችን የራስን ገቢ ማመንጨት፣ ተወዳዳሪና በደንበኛ ተወዳጅ መሆን እንዲሁም ለአካባቢው ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ለዚህም የግለሰቦች የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የተቋምን ለውጥ ስለሚያመጣ የበላይ አመራሩ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ መሥራት እንደሚገባ እና በቀጣይም ለሁሉም የተቋሙ መምህራንና ሠራተኞች ተመሳሳይ ግንዛቤ በማስጨበጥ የጋራ ራእይ እንዲኖር ለማስቻል ሥልጠናውን የመስጠት ዕቅድ እንደተያዘ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት አሠልጣኝና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ አበበ ሥልጠናው ፐብሊክ ኢንተርፕሪነርሺፕ፣ ፈጠራ ምኅዳር ግንባታ ላይ መሰጠቱን ጠቁመው በኢትዮጵያ እንደ ሀገር ኢንተርፕሪነሪያል ትግበራን ለመገንባት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና እንዲኖራቸው ግለሰባዊ የአመለካከት ለውጥ፣ የሥራ ፈጠራና የፐብሊክ ኢንተርፕሪነሪያል ባህርይን መላበስ የሥልጠናው ትኩረት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አሠልጣኙ ሥልጠናው ሠልጣኞች የሥራ ፈጠራን ማበልጸጊያ ዘዴዎች፣ ችግሮችን የመለየት፣ መፍትሔ የማበጀት እና ግለሰባዊ የሥራ ብቃትን የናማጎልበትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በራሳቸው አቅም ማከናወን እንደሚችሉ ያዩበት እንዲሁም የተቋሙን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሃሳቦችን ያቀረቡበት ነው ብለዋል፡፡

የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንትና የሥልጠናው ተሳታፊ ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ሥልጠናው ያለንን ሀብት በመጠቀም ዩኒቨርሲቲውን ኢንተርፕሪነሪያል/entrepreneurial/ ለማድረግ ግንዛቤያችንን ያሳደግንበትና ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ በበኩላቸው ሥልጠናው በተቋም ደረጃ ከመንግሥት ድጎማና በጀት በመነሳት ወደ ራስ ገዝ ለመምጣት መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታና ተግባር ወደ መሬት ለማውረድ ከፍተኛ የሆነ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ገ/መድኅን ጫሜኖ ሥልጠናው ከፍተኛ መነሳሳትን እንደፈጠረባቸው ተናግረው ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት የአመለካከት ለውጥ በማምጣት የተቋሙን የሰው ኃይልና በጀት በማቀናጀት መሠረተ ልማቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ሥልጠናው ጉልህ ፋይዳ ያለው ስለመሆኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት