Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የብዝሃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል “Molecular Characterization, Nutritional Profiling, Biological activities, and Value-Chain of Moringa stenopetala from Southern Ethiopia” በሚል ርዕስ የሚሠራ ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ኅዳር 14/2016 ዓ.ም ይፋ አድርጓል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝደንት ተ/ፕ  በኃይሉ መርደኪዮስ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ሞሪንጋ በአከባቢያችን በስፋት የሚበቅልና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ተክል ሲሆን በተክሉ ላይ ይበልጥ ምርምር ማከናወንና ማስተዋወቅ ይገባል፡፡ ሞሪንጋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅምና ዘርፈ ብዙ የጤና ጥቅሞች ያሉት ተክል መሆኑን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ ይፋ የተደረገው ግራንድ የምርምር ፕሮጀክትም ተክሉ የሚገባውን ያህል ጥቅም እንዲሰጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ የግራንድ ፕሮጀክቱ ሥራ ውጤቶች ምርቱን በመሰብሰብ፣ እሴት መጨመርና የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን በማበልጸግም የሥራ ዕድል በመፍጠር አምራች አርሶ አደሮች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙና አኗኗራቸው እንዲሻሻል ጉልህ አስተዋጽዖ ማበርከት ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ረ/ፕ አዘነ ተስፋዬ እንደገለፁት የሞሪንጋ ተክል እንደየአከባቢው በባህላዊ መንገድ ለተለያዩ በሽታዎች መድኃኒትነት፣ ለምግብነት፣ ለአፈር ጥበቃና ለውበት መጠበቂያነት የሚውል ነው፡፡ ሞሪንጋ 14 ዓይነት ዝርያዎችን የያዘ ሲሆን በኢትዮጵያ ሁለቱ ማለትም “Moringa stenopetala/ሞሪንጋ ስቴኖፔታላ/ እና ሞሪንጋ “Moringa oleifera/ሞሪንጋ ኦሊፍራ/ ብቻ ለጊዜው ታውቀው በኅብረተሰቡ ዘንድ ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ Moringa stenopetala/ሞሪንጋ ስቴኖፔታላ/ የሚባለው በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አከባቢ በስፋት የሚገኝ የተክሉ ዓይነት መሆኑንም ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በሚገኘው ሠርቶ ማሳያ 50 የሞሪንጋ ስቴኖፔታላ አክሴሼንስ/Moringa stenopetala accessions/ ተሰብስበው ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን የገለጹት ረ/ፕሮፌሰሩ በነዚህ ዝርያዎች ላይ ምርምሮችን በማካሄድ ከተለያዩ መመዘኛዎች አንፃር የተሻሉትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መለየት የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት እንደሆነ አውስተዋል፡፡ ከፕሮጀክቱ ስፋት አንፃር ለሥራው ማስፈጸሚያ 3.5 ሚሊየን ብር የሚያስፈልግ በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው ከተመደበው 1.75 ሚሊየን ብር በተጨማሪ ቀሪውን ከደጋፍ ድርጅቶች ገንዘብ ለማግኘት ይሠራል ብለዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምር ዓይነቶች እንዳሉ ተናግረው ይህኛው ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ሲሆን የማስተርስ ተማሪዎችን እንዲሁም ከምርምር ባሻገር የማኅበረሰብ ጉድኝትን አካቶ የሚሠራ ነው፡፡ ሞሪንጋ ላይ ለሚሠራው ፕሮጀክትም ዩኒቨርሲቲው አንድ ሚሊየን ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በጀት የመደበና ፕሮጀክቱ የአምስት ዓመት ቆይታ ያለው መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ፣ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሜንድል ዩኒቨርሲቲ/Mendel University/፣ ከስዊዲን ግብርና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ/Swedish University of Agricultural Sciences/፣ ከቼኮዝላቪያ የሕይወት ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ/Czech University of Life Sciences/ የተጋበዙ እንግዶች  ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ በትብብር ለመሥራት ፈቃደኛና ቁርጠኛ መሆናቸው የገለጹ ሲሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘውን የሞሪንጋ ምርምር ሠርቶ ማሳያም ጎብኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት