Print

የዩኒቨርሲቲው የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በጋሞ ዞን ገረሴ ዙሪያ ወረዳ የእንስሳት መኖ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እና የአፈር ለምነትን መጠበቅ ላይ የሚሠራ የምርምር ሜጋ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ታኅሣሥ 09/2016 ዓ/ም በገረሴ ከተማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ ዞኑ ካለው ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ቁጥር አንጻር የምርምር ፕሮጀክቱ የሚሰጠው ጠቀሜታ ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡ ዶ/ር ደግፌ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በተሻሻሉ የቡናና የበቆሎ ዝርያዎች ላይም በወረዳው የምርምር ሥራ ማከናወኑን በማስታወስ በቀጣይም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በእንስሳት ሳይንስ ት/ክፍል መምህር፣ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መ/ር ዮሐንስ ዳና እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የተለያዩ የመኖ ዝርያዎችን በመቀየጥ የንጥረ ምግብ ይዘታቸውን መለየት፣ በምርምር የተገኙ የመኖ ዝርያዎችን ለእንስሳት በመመገብ የሚታየውን ለውጥ ማየት እንዲሁም የመኖ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የገረሴ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን ካማ ወረዳው በምርትና ምርታማነት ዙሪያ ከፍተኛ ችግር ያለበት እና የአርሶ አደሩ ሕይወት ከእጅ ወደ አፍ  የምርምሩ ተጠቃሚዎች በመሆናችን ለዩኒቨርሲቲው ያለን ምስጋና የላቀ ነው ብለዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ በመግለጽ በወረዳው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በወረዳው ደጋማ፣ ቆላማና ወይና ደጋማ አየር ንብረት ላይ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን በእርሻ ቦታ ምርጫ ትብብር እና በመረጃዎች ልውውጥ አስፈላጊነት ዙሪያ መግባባት ተደርሷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት