Print

በኢትዮጵያ የሲቪል ምህንድስና ተማሪዎች ማህበር ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በወቅታዊ የሲቪል ምህንድስና ሥራ ልምዶች ላይ ያተኮረ ሲምፖዚዬም ግንቦት 4/2006 /ም ተካሂዷል፡፡ በሲምፖዚዬሙ ከሲቪል ምህንድስና ጋር የተያያዙ ሙያዊ ጉዳዮችን በሚመለከት በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህራንና ተማሪዎች የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርና የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት በአገራችን በምህንድስናው መስክ በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተጽዕኖዎች መጎልበት በመቻላቸው የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው ከማደጉም አልፎ ለምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ስኬት የበኩሉን በመወጣት ላይ ነው፡፡ ኢንደስትሪው በግልም ሆነ በመንግሰት የሚጠይቀው የሰው ኃይል በእጅጉ በመጨመሩ በዘርፉ በእውቀትና በክህሎት የዳበሩ ባለሙያዎችን ማፍራት ወሳኝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ይህን መሰል ፎረሞች መዘጋጀታቸው ሙያዊ አቅምን ለማሳደግና እርስ በእርስ ለመማማር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ የልማት ህዳሴ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረጉ ረገድ በሲቪል ምህንድስና የሙያ መስክ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ሚና የጎላ በመሆኑ ማህበሩ ይህን ለመደገፍና አቅማቸው እንዲጎለብት ለማድረግ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በሲምፖዚዬሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ በቴክኖሎጂ ኢንሲትቲዩት የሚገኙ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ መምህራን እንዲሁም የሲቪል ምህንድስና የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ150 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ምህንድስና ተማሪዎች ማህበር በ2004 /ም ህጋዊ እውቅና አግኝቶ የተቋቋመ ሲሆን የዘርፉ ተማሪዎች ከሙያው የሚጠበቀውን ክህሎት እንዲያገኙ በማድረግ በታማኝነትና በጥሩ ስነ-ምግባር የታነፁ እንዲሁም የበቁ ምሁራንን በማፍራት ያደገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችል ራዕይን አንግቦ የሚንቀሳቀስ ማህበር ነው፡፡