Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በጅማ የእርሻ ምርምር ማዕከል ትብብር በጋሞ ጎፋ ዞን ከሚገኙ ሦስት የቡና አብቃይ ወረዳዎች አንዱ በሆነው ካምባ ወረዳ ላገፎ ቀበሌ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲካሄድ በነበረው የቡና ምርምር ፕሮጀክት አፈፃፀምና የጥናት ግኝት ላይ ኅዳር 7/2010 ዓ/ም የመስክ ጉብኝትና የምርምር ውጤቶች ትውውቅ ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የመስክ ጉብኝቱ ዓላማ በዞኑ ቡና አብቃይ ወረዳዎች በተደረጉ ጥናቶችና ከባቢያዊ ሥነ-ምህዳር ዓይነቶች መነሻ ነባሩን የአካባቢ ዝሪያ ‹‹አርሞ›› ጨምሮ በሌሎች ሦስት ዝሪያዎች ምርምር ውጤቶች ላይ ምልከታ ማድረግና ቀደም ሲል በአካባቢው ያለውን የአመራረት ዘዴና አፈፃፀም ዝርዝር ማወቅ ነው፡፡ በዚህም ተመሳሳይ ሥነ-ምህዳር ያላቸውን ቀበሌያት በመውሰድ ከቀበሌያቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ በመተግበርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩ በዘርፉ ተጠቃሚነቱን እንዲያሰፋ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የብዝሃ-ህይወት ማዕከል ዳይሬክተርና የዘርፉ ተመራማሪ መ/ር ሰይፉ ፈቴና ገልፀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በመክፈቻ ንግግራቸው በሀገራችን በተለይም በቡና አብቃይ አካባቢዎች ቡና መስጠት የሚገባውን ያህል ጥቅም እያስገኘ አለመሆኑን በመግለጽ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት ዘርፉን በጥናትና ምርምር ማገዝና ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ በዞኑ ቡና አብቃይ አካባቢዎች ከፍተኛ በጀት በመመደብ እየሠራ መሆኑንና በተገኘው መልካም ውጤት መነሻነትም ሥራውን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በካምባ ወረዳ አርሶ አደሩ ተለምዷዊ አሠራርን ተከትሎ በማምረቱና በጥናትና ምርምር የተደገፈ ምርጥ ተሞክሮ ማስፋፋት ባለመቻሉ ተጠቃሚነቱ እምብዛም ሆኖ መቆየቱን የወረዳው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊና የወረዳው አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ተስፋጽዮን ዘነበ ገልፀዋል፡፡

የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የቡና ምርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ባለፈ 25 በመቶ ለሚሆነው ህዝብ የኑሮ መሠረት መሆኑን በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እንዲህም ሆኖ ዘርፉ በጥናትና ምርምር ባለመደገፉ  በዝሪያ አጠቃቀምና በምርት አያያዝ ችግር በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ ሆኖ ኢኮኖሚውን መደገፍ ያልቻለ ሲሆን ሽፋኑም በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የተገደበ እንደሆነ የፕሮጀክቱ ተመራማሪዎች አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለፃ በቡና አብቃይ ወረዳዎች የሚታየው የቡና ምርትና ምርታማነት ከ5-6 ኩንታል በሄክታር ሲሆን  ይህም በብሔራዊ ደረጃ ካለው ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ ለዚህም በአርሶ አደሩ ጓሮ የተተከሉ ጥቂት የቡና እናት ዛፎች ነባር ዝሪያዎች በመሆናቸው በቀላሉ በበሽታ መጠቃታቸውና በቂና የማያቋርጥ የዘር ምንጭ አለመኖር በዋናነት የዘርፉ እንቅፋት እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ አዲስ የተሻሻሉ ዝሪያዎች ከዘር ዝግጅት አንስቶ አራት ዓመት ተኩል የሚወስዱና በተተከሉ በሦስተኛ ዓመታቸው ምርት መስጠት የሚጀምሩ ሲሆን ከአራቱ ዝሪያዎች በተለይም 74158 እና 74110 የተባሉ በዓመት ሁለት ጊዜ ምርት የሚሰጡና በሄክታርም ከ12-25 ኩንታል ምርት ማምረት የሚያስችሉ ናቸው፡፡

በመስክ ጉብኝቱ የተገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት በቡና ምርት ሂደት የዝሪያ አማራጭ አጠቃቀም በዕውቀትና በሣይንሳዊ መንገድ ሳይደገፍ ለዘመናት በመተግበሩ ምርትና ምርታማነቱ ላይ አያሌ ችግሮች እንደገጠሟቸውና ውጤታማም እንዳልነበሩ ገልፀው በአካባቢያቸው በተቋቋመው የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጣቢያ የታየው ውጤትና የዘር አማራጭ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ ወደየቀበሌያቸው ሲመለሱም ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች ለማጋራትና  የዘር ማፍላቱ ሥራ ተጠናቆ ሲሠራጭ ለመጠቀምና ምርታማ ለመሆን ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠው ለዚህም የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንዳይለያቸው አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በግብርና ሣይንስ ኮሌጅ በእጽዋት ሣይንስ ትምህርት ክፍል አነሳሽነት ከጅማ እርሻ ምርምር ማዕከል ጋር በመቀናጀት በ2005 ዓ/ም የተጀመረው ፕሮጀክት ከ400 ሺህ ብር በላይ በጀት በዞኑ ሦስት ወረዳዎች ስድስት የምርምር ጣቢያዎች ተቋቁመው ዘርፉን በጥናትና ምርምር የመደገፍ  ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የብዝሃ-ህይወት ማዕከል፣ በጅማ የእርሻ ምርምር ማዕከልና በከምባ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፅ/ቤት አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ተመራማሪዎች፣ የጅማ እርሻ ምርምር ማዕከል ባለሙያዎችና የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ የካምባ ወረዳ አመራሮችና የገጠር ግብርና ጣቢያ ባለሙያዎች እንዲሁም ከ18ቱ የወረዳው ቀበሌያት የተወጣጡ ሞዴል አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡