Print

ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው የ2008 ዓ.ም አዲስ ገቢ ተማሪዎች በ20/02/08 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
ሥልጠናዎችን መስጠትና በዩኒቨርሲቲው የሚፈፀሙ ብልሹ አሠራሮችን ተከታትሎ በማስረጃ በማስደገፍ ለሚመለከተው አካል ማድረስ የዳይሬክቶሬቱ አበይት ተግባራት መሆናቸውን ተወካዩ አቶ ዮሴፍ ወርቁ ገልፀዋል፡፡ በዕቅድ ከተያዙ ሥልጠናዎች አንዱ የሆነው የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ሥልጠና ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በሥነ-ምግባር ታንፀው የመጡበትን የትምህርት ዓላማ በአግባቡ እንዲያሳኩ የሚረዳቸው ነው፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ችግሮች ሲገጥሟቸው እንዴት መፍታት እንደሚችሉም ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡
የሥነ-ምግባር ምንነት፣ በዩኒቨርሲቲው የሚከሰቱ ብልሹ አሠራሮችን ለመታገል ተማሪዎች ያላቸው ሚና፣ ከመማር ማስተማር ጋር በተያያዘ በተማሪዎችና በመምህራን የሚፈጠሩ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው፣ የተማሪዎች መብትና ግዴታ፣ ከህግና ደንብ አከባበር እንዲሁም ከንብረት አያያዝ አንፃር የሥነ-ምግባር ጉድለቶች በሥልጠናው የተዳሰሱ ርዕሶች ናቸው፡፡
ሠልጣኞቹ በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርሲቲው የሚኖራቸው ቆይታ ሠላማዊ እንዲሆንና በሥነ-ምግባር እንዲታነፁ ሥልጠናው አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከምግብና ህክምና አገልግሎት እንዲሁም ከውጤት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ  ጥያቄዎችን አንስተው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ሥልጠናው በመምህራንና በዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን 2,416 አዲስ ገቢ ተማሪዎች በየካምፓሶቻቸው ተሳትፈዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት