Print

በ2008 የትምህርት ዘመን አንደኛ መንፈቀ ዓመት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች የሽልማት ፕሮግራም በ15/08/08 ዓ.ም በኮሌጁ ግቢ ተካሂዷል፡፡

 

ከህክምና፣ ጤና መኮንን፣ ነርሲንግ፣ ሜዲካል ላቦራቶሪ፣ ሚድዋይፍሪ፣ አኒስቴዢያ እና ሜዲካል ራዲዮሎጂ የትምህርት ክፍሎች ከእያንዳንዱ ባች የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከየትምህርት ክፍሉ የተሻለ ውጤት ያላቸው ሴት ተማሪዎችም በልዩነት ተሸልመዋል፡፡

የፕሮግራሙ ዓላማ በውጤታቸው ብልጫ ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና በመስጠት ማበረታታትና ለበለጠ ሥራ ማነሳሳት እንዲሁም ሌሎች ተማሪዎች አርአያቸውን በመከተል እንዲነቃቁ ማድረግ መሆኑን የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ም/ዲን እና የዲን ተወካይ ወ/ሮ መቅደስ ቆንዳሌ ገልፀዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ የተመዘገበውን መልካም ውጤት ለማስቀጠል እንዲሁም ሌሎች በርካታ ተሸላሚዎችን ለማፍራት የመረዳዳት መንፈስን ማዳበርና በትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት መጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ተሸላሚ ተማሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ሽልማቱ የበለጠ ለመሥራት የሚያነሳሳ እና በተማሪዎች መካከል ጤናማ የፉክክር መንፈስን የሚያዳብር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የህክምና ሙያ ከሰው ህይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በእውቀት፣ በከፍተኛ ጥንቃቄና በመልካም ሥነ-ምግባር ሊከናወን ይገባል ያሉት ተማሪዎቹ በዚህ ረገድ የኮሌጁ ተማሪዎች ለሌሎች አርአያ መሆን እንሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

በፕሮግራሙ በድንገተኛ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው የ4ኛ ዓመት የጤና መኮንን ተማሪ መሐመድ ሸሪፍ ረመዳን እንዲሁም በቅርቡ በጋምቤላ ክልል በደቡብ ሱዳን ታጣቂ ቡድን ህይወታቸውን ላጡ ንፁሃን ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎትና የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡