Print

ዩኒቨርሲቲው 45 የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ተማሪዎችን የካቲት 25/2009 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 40ዎቹ ወንዶች ሲሆኑ 5ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ከተመራቂዎቹ መካከል 3.61 በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ክፍለማርያም ጌታነህ በ1ኛነት፣ 3.52 በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ መስፍን ውሂብ በ2ኛነትና 3.49 በማምጣት የማዕረግ ተመራቂ አቤል ዓይናለም በ3ኛነት ሲሸለሙ 2.96 በማምጣት ተመራቂ ቤተል ተሾመ ከሴቶች በአንደኛነት ተሸላሚ ሆናለች፡፡

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ፕሬዝደንት ተወካይና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ኢ/ር ውብሸት ብርሃኑ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ መንግሥት የከተሞች ልማትን ለማፋጠን ከፍተኛ በጀት መድቦ በልዩ ትኩረት በመሥራት ላይ የሚገኝ በመሆኑ መጪው ጊዜ ለአርክቴክቶች ሰፊ ዕድልን የያዘ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ተመራቂዎች ይህንን ዕድል በመጠቀም በሀገራቸው የከተማ ልማት የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ አሳስበዋል፡፡

አርክቴክቸር ባህል፣ ታሪክና ኢኮኖሚክስን የሚያቅፍ እንዲሁም ያለፈው፣ የአሁኑ እና የመጪው ጊዜ አገናኝ ድልድይ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ኢ/ር ውብሸት በሁሉም ዘርፍ የላቀ መሆን ከባድ ቢሆንም ክህሎት ያለው አርክቴክት የተለያዩ ሙያዎችን  በማጣመር አካባቢውን ለመገንባት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት መቻል አለበት ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ተመራቂዎች ከዩኒቨርሲቲው የገበዩትን እውቀትና ክህሎት ከነባራዊው የሥራ ዓለም ልምድ ጋር በማጣመር በተመረቁበት ዘርፍ ብቁ ባለሙያ መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ከተሞችን ለነዋሪው ምቹ፣ ጽዱና ውብ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ በሚገኝበት ወቅት በመመረቃችሁ በዘርፉ የበኩላችሁን ድርሻ ለመወጣት ራሳችሁን ማዘጋጀት ይጠበቅባችኋልም ብለዋል፡፡

የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል በ1997 ዓ/ም የተቋቋመ ሲሆን በሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን የተማሪዎች ዲዛይን ውድድሮች በመሳተፍ በ2007 ዓ/ም የሁለተኛነት እንዲሁም በ2008 ዓ/ም ከ17 ዕጩዎች የአንደኛነት ደረጃ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ግንባታው በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአርክቴክቸር ዲዛይን ስቱዲዮም ትምህርት ክፍሉ ይበልጥ ተጠናክሮ ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን እንዲያፈራ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል፡፡