የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከጋሞ ጎፋ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ጋር በመተባበር ከዞኑ ባ/ቱ/መ/ኮ/ጉ መምሪያ እና ከ15ቱ ወረዳዎችና ከ2ቱ ከተማ አስተዳደሮች ባ/ቱ/መ/ኮ/ጉ ጽ/ቤቶች ለተወጣጡ 41 የባህልና ቋንቋ ጥናት ባለሙያዎች ከመጋቢት 11 - 13/2009 ዓ.ም የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ 

ስልጠናው የቋንቋ ምንነት፣ ተግባራት፣ ፖሊሲና ዕቅድ እንዲሁም ታሪካዊ አመጣጡን ሠልጣኞች ለይተው እንዲያውቁ የሚያደርግ እና በማኅበረሰብ ፎክሎር፣ ባህልና እሴቶች ዙሪያ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን የማኅበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ተወካይ መ/ር አራጋው ደለለ ገልፀዋል፡፡ ከዘርፉ የጥናት ባለሙያዎች  ግብዓት የሚሰበሰብበትና የሚጠናከርበትም ነው ብለዋል፡፡

ሥልጠናው በማኅበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ሥር በሚገኙ ሦስት ትምህርት ክፍሎች መ/ራን የተሰጠ ሲሆን በቋንቋ ጥናትና ዶክመንቴሽን ፅንሰ ሃሳብና የጥናት ዘዴ እንዲሁም በባህል ጥናትና የማኅበረሰብ ፎክሎር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ቋንቋ፣ ባህልና እሴቶች መገለጫቸው ቢለያይም የእርስ በርስ ግንኙነት ያላቸውና በህዝቦች መሰረታዊ አኗኗር መልካም ግንኙነት በመፍጠር፣ ችግሮችን በጋራ እንዲፈቱ በማድረግ እንዲሁም ሀገረሰባዊ ቅርሶችና ባህላዊ ትውፊቶችን በመንከባከብና በመጠበቅ ለማኅበራዊ ልማት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡

ዞኑ አምስት ብሔረሰቦችን የያዘ በመሆኑ ቋንቋውን፣ ባህሉንና እሴቶቹን ይበልጥ ለይቶና አውቆ በአግባቡ መጠቀም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር ልማቱ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን  አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን የጋሞ ጎፋ ዞን ባ/ቱ/መ/ኮ/ጉ/መምሪያ ኃላፊ አቶ ካምቦ ዴሮ ተናግረዋል፡፡፡፡ ስለሆነም በሥልጠናው የሚገኘውን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር መለወጥና በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

ሰልጣኞች በአስተያየቶቻቸው ስልጠናው ትኩረት የሚስብና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በቋንቋና ባህል ዙሪያ በርካታ ሃሳቦችና ጥያቄዎችን አንስተው በአሰልጣኝ መምህራን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በስልጠናው መጨረሻ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡