ሠላም ፎረም ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ጋር በመተባበር ለፎረሙ አባላትና ለባለድርሻ አካላት በሠላም ምንነትና አስፈላጊነት፣ በግጭት ፅንሰ ሃሳብ እንዲሁም በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ላይ ከመጋቢት 15-16/2009 ዓ/ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የፎረሙ አባላትና ባለድርሻ አካላት በሠላም ምንነትና አስፈላጊነት፣ በግጭት ፅንሰ ሃሳብና በግጭት አፈታት ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በማዳበር ሠላማዊ መማር ማስተማር እንዲሰፍን ማስቻል የስልጠናው ዓላማ መሆኑን በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሠላም ፎረምና የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ የመረጃ አስተባበሪ አቶ ኃይሉ ማቲዎስ ገልፀዋል፡፡ በነገሮች ላይ የሚኖረን የተዛባ አመለካከትና ውሳኔ የእርስ በእርስ ብሎም ሀገራዊ ግጭት ውስጥ ሊከተን ስለሚችል የሚገጥሙ ችግሮችን በሰከነ መንፈስ በመረዳትና አመለካከቶችን በማስተካከል ሠላምን ማስጠበቅ የሚገባ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ሠላምን የማስጠበቅ ተግባር የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ሠልጣኞች በስልጠናው ያገኙትን የሠላም እሴት ግንባታ ዕውቀት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በማካፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡና ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በተሻለ ሁኔታ የሰፈነበት ተቋምን ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡

በስልጠናው የሠላም ፎረም አባላት፣ የተማሪዎች ህብረት አባላት፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና የኮሌጅ ዲኖች ተገኝተዋል፡፡

ሠላም ፎረም በ2006 ዓ/ም የተቋቋመ ሲሆን ተማሪዎች እርስ በእርስ፣ ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሠራተኞች እና ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት እንዲያጎለብቱ መርዳት እንዲሁም ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ የመፍታት አመለካከቶችን ማዳበር ከፎረሙ ዓላማዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡