በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ ህንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት/EIABC/ በመጡ ተጋባዥ ምሁራን "የከተሞችን ዲዛይን የተሻለ ማድረግ›› እና ‹‹አርክቴክቸርና የከተማ ፕላን ለዘላቂ ልማት የሚያደርገው አስተዋፅኦ" በሚሉ ርዕሶች ጥር 5/2009 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የከተሞች ፕላን እንዲኖርና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ሀገሪቱን ዘመናዊ፣ ለኑሮ ተመራጭና የተሻለ የከተማ ዲዛይን ያላት እንድትሆን ለማስቻል ውይይቱ መዘጋጀቱን የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መ/ር ግዛው ፍቅሬ ገልፀዋል፡፡ ትምህርት ክፍሉ ከበርካታ የትምህርት መስኮች ጋር ቁርኝት ያለው በመሆኑ ተማሪዎች አዳዲስ ሀሳቦችንና ግኝቶችን እንዲያፈልቁና ጥናትና ምርምሮቻቸው ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ለማስቻል እንዲሁም ለሚስተዋሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣትም አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ በዘርፉ ያለውን የተማረ ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሠራ የሚገባ መሆኑን መ/ር ግዛው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ህንፃ ግንባታ እና የከተማ ልማት ኢንስቲትዩት ተጠሪ ዶ/ር ኤሊያስ ይትባረክ ‹‹የከተሞችን ዲዛይን የተሻለ ማድረግ›› በሚል ርዕስ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ የኢትዮጵያ ከተሞች ፈጣን ዕድገት እያስመሀገቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአንፃሩ ዕድገቱን ተከትሎ በከተሞች አካባቢ የህዝብ ቁጥር አለመመጣጠን፣ ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት፣ ህገ-ወጥ ግንባታ፣ ከቦታ ጥበት ጋር ተያይዞ በከተማው አውራ መንገዶች ላይ አላስፈላጊ የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ ተሽከርካሪዎች ያለስፍራቸው መቆም እና መሰል ችግሮች የሚስተዋሉ መሆኑን በምስል አስደግፈው  አሳይተዋል፡፡

‹‹አርክቴክቸርና የከተማ ፕላን ለዘላቂ ልማት የሚያደርገው አስተዋፅኦ›› የሚል ጽሑፋቸውን ያቀረቡት መ/ር ዮናስ አለማየሁ የከተማ ፕላን ከዘላቂ ልማት ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት አስረድተዋል፡፡ ከመሠረተ ልማት ዕድገት ጋር ተያይዞ የለውጦች መታየት በዋናነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑንም ቃኝተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል መምህራንና ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ተጋባዥ ምሁራኑ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ያካበቱትን የረጅም ጊዜ ልምድ አካፍለዋል፡፡ ከተሳታፊዎች በተነሱ አስተያየትና ጥያቄዎች ላይ በጋራ ውይይት በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ይሆናሉ ባሏቸው ነጥቦች ላይም አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡